የኮምፒውቲንግና ኢንፎርማቲክስ ኮሌጅ እና ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬት ከማህበረሰብ ተኮር ትምህርት ዳይሬክቶሬት ጋር በመተባበር ለአከባቢው ማህበረሰብ ትምህርት ቤቶች መምህራን ለ3ት ቀናት የቆየ ስልጠና ሰጠ

 

ስልጠናው በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ አከባቢ ያሉ  2ኛ ደረጃ እና መሠናዶ ት/ቤቶች እንድሁም ከቴክኒክና ሙያ ተቋም ለተውጣጡ  50 መምህራን የተሰጠ ሲሆን በዋነኛነት በ ICT ዙሪያ ሙያቸውን ከፍ ለማድረግ ታስቦ መሆኑን በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ተሳትፎ እና የኢንተርፕራይዝ ልማት ም/ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ከበደ ወልደፃዲቅ ገልፀዋል።

IMG_6980 IMG_6978

ወደ ስልጠናው ከመገባቱ በፊት የዳሰሳ ጥናት የተካሔደ ሲሆን የ ICT መሳሪያዎች አቅርቦት እና አጠቃቀም ላይ ከየትምህርት ቤቶቹ ዳይሬክተሮች እና መምህራን ጋር ውይይት ተደርጎ የመፍትሔ አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ጉታ ገልፀዋል።በዚሁ መሠረት የዳሰሳ ጥናቱ የተደረገባቸው ትምህርት ቤቶችም አደሌ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ፣አወዳይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ፣ሐረማያ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ፣ባቴ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ፣ሐረማያ ሁለተኛ ደረጃና መሠናዶ ት/ቤት ፣የሐረማያ ቴክኒክ እና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋም እንድሁም በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚገኘው ሞዴል ት/ቤት መሆናቸውን ለሐ.ዩ ኤፍ ኤም 91.5 ተናግረዋል።

በተመሳሳይ መልኩ በትምህርት ቤቶቹ ውስጥ የተበላሹ የ ICT መሳሪያዎችእንዳሉ በመጠቆም 12 ኮምፒውተሮች፣ 3 ፎቶ ኮፒ ማሽኖች እና ፕሪንተሮች ጥገና የተደረገላቸው መሆኑን ገልፀው ከ 20,000 (ሀያ ሺህ ብር) ያላነሰ የገንዘብ ወጪ እንዲያተርፉ ትምህርት ቤቶቹን የረዳቸው መሆኑን የኮምፒውቲንግና ኢንፎርማቲክስ ኮሌጅ ዲን አቶ ሰይፉ ነዳ ከሬድዮ ጣቢያችን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልፀዋል።

ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል ካናገርናቸ ውስጥ መምህር እንዳለ መኮንን ( በሐረማያ ሁለተኛ ደረጃ እና መሠናዶ ት/ቤት የ IT መምህር) እንደተናገረው ከሆነ ከስልጠናው ብዙ እውቀቶችን ያገኘ መሆኑን ገልፆ በተለይም ፕሪንተር እና ፎቶ ኮፒ ማሽን ጥገና ላይ ያገኘሁት ክህሎት ከዚህ በፊት የማላውቀው ነው በማለት ተናግሯል።

IMG_6970 IMG_6967

ሌላኛዋ መጠይቅ ያደረግንላት የስልጠናው ተሳታፊ የሆነችው ትዕግስት እንደተናገረችው ከሆነ በትምህርት ቤታቸው በ ICT  ዙሪያ ክህሎት ከማነስ የተነሳ ያጠቃቀም ክፍተት ያለ መሆኑን በመግለፅ በዚህ አጭር ቀናት ውስጥ ትልቅ ክህሎት ማግኘቷን ገልፃለች።በተጨማሪም መሰረታዊ የኮምፒውተር አጠቃቀም እውቀትለሁሉም አስፈላጊ ከመሆኑም ባሻገር ሌሎች እውቀቶችንም ጭምር ማግኘት እንዳለባቸው ተናግራለች።

በመጨረሻም ለሰልጣኞች የተሳትፎ የምስክር ወረቀት ከሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ክቡር ዶክተር ግርማ አመንቴ እጅ የተቀበሉ ሲሆን ተሳታፊዎች ያገኙትን እውቀት ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው በመዝጊያው ስነስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር ገልፀዋል።

አዘጋጅዘይኑ ሚስባህ እድሪስ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

HTML tags are not allowed.