የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ክቡር ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ንግግር

 

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲና ህንድ አገር ከሚገኝ ቢ ኤም ቪ ኤስ ኤስ ከተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር በምስራቅ ኢትዮጵያ አጎራባች ክልሎች ለሚገኙ 300 አካል ጉዳተኞች የሰው ሰራሽ እግር ተከላና የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የመሰረት ልማት ማስፋፊያ ፕሮጀክት ምረቃ ላይ የተደረገ ንግግር


የተከበራቸሁ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፤

የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ፤

የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አካላትና ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች እንኳን ደህና መጣችሁ! እንደምን ቆያችሁ!

ሀገራችን ኢትዮጵያ ከምትገኝበት የኢኮኖሚ ደረጃ ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ ለማድረግ መንግስታችን ዘርፈ ብዙ ዕቅዶችን በመንደፍና በመተግበር ተጨባጭ የሆነ ዕድገት እያስመዘገበ ይገኛል፡፡ እየተመዘገበ ያለውን ዕድገት በዘላቂነት እንዲቀጥል ለማስቻል፤ የ2ኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን በማዘጋጀትና በመተግበር ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገም ይገኛል፡፡ ይህ ዕቅድ የሁሉንም ዜጎች እኩል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚያስችል ሁኔታ የተዘጋጀ ሲሆን አፈፃፀሙም ይህንኑ መሰረት አድርጎ እየተተገበረ ይገኛል፡፡

በዚህም በዕቅዱ የማህበራዊ ደህንነትን ለማረጋገጥ ለአካል ጉዳተኞች፣ አረጋዊያንና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችን የዴሞክራሲያዊና እና ሰብአዊ መብቶች እኩል ጥበቃ ለማድረግ እና በልማቱ  እኩል ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማስቻል  ከአገሪቱ ህገመንግስት ጀምሮ በበርካታ የዓለም አቀፍ ስምምነቶች እና አገራዊ ህጎች ተረጋግጦ ለተግባራዊነቱም መንግስት ከአያሌ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ እስካሁን የተደረገው ጥረት በሚፈለገው ደረጃ ያልደረሰ ቢሆንም፤ የአገራችን ዜጎች ብሎም የአካል ጉዳተኞች የትሩፋቱ ተጠቃሚ መሆን ጀምረዋል፡፡ የሚፈለገውን ዉጤት ለማግኘትና የዜጎችን በተለይም የአካል ጉዳተኞችን የማህበራዊ ዋስትና አገልግሎት ሽፋን ለማሳደግ የሚረዱ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ፡፡

ከዚህም በተጨማሪ መንግሰት የአካል ጉዳተኞችን የአካላዊ ተሃድሶ አገልግሎት ተጠቃሚ የሚሆኑበትንም ዕቅድ በመተግበር የአካል ጉዳተኞችን ችግር ለማቃለል ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀስቀስ ላይ ይገኛል፡፡የአካል ጉዳተኞችንም ችግር ለማቃለል መንግስት ልዩ ትኩረት በመስጠት በሁሉም ክልሎች ውስጥ የአካል ጉዳተኞችን ችግር የሚከታተልና መፍትሄ የሚሰጥ እንዲሁም የተለያዩ ድጋፎችን የሚያሰባስብ መዋቅር እንዲዘረጋ አድርጓል፡፡

 

የአካል ጉዳተኝነት በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት ሊከሰት የሚችል በመሆኑ፤ ኀብረተሠባችንን ባሳተፈ መልኩ በሰው ሰራሽ አደጋዎች የሚከሰቱ የአካል ጉዳተኝነት ለመቀነስና በአካል ጉዳተኞች ላይ የሚደርሱ የተለያዩ ተፅዕኖዎችን ለመቀነስ መንግስት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የግንዛቤ ማሳደጊያ ሥራዎችንና የተለያዩ ድጋፎችንም በተለያዩ አካባቢዎች በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

ዩኒቨርሲቲዎች ለሚገኙባቸው አካባቢዎች በተለያዩ ዘርፎች የማኀበረሰብ አገልግሎት መስጠት ከተልዕኳቸው አንዱ በመሆኑ የአካል ጉዳተኞችን ችግሮች በማቃለል ረገድ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲያበረክቱ ይጠበቃል፡፡ ከዚህ በፊት በአገራችን አካል ጉዳተኞች የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ገብተው የመማር እድል ያገኙ የነበሩት በጣም ጥቂት ሲሆኑ ይህንንም አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው በአንድ ዩኒቨርሲቲ ብቻ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ባለፉት አስር ዓመታት መንግስታችን የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሲባል በሰጠው ልዩ ትኩረት በበርካታ የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አካል ጉዳተኞች የትምህርት እድል እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲም የአካል ጉዳተኞችን የትምህርት መብት ለማረጋገጥ የሚረዱ በርካታ ሥራዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡ ለአብነትም ያህል ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የሆኑ የመማሪያ ክፍሎች፣ የመኖሪያ ቤቶች እና እንዲሁም ልዩ የማንበብያ ክፍሎችና ቁሳቁሶችን በማሟላት ትምህርታቸውን በአግባቡ ተከታትለው በቂ እውቀት ጨብጠው እንዲወጡ ከፈተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡

እነሆ ዛሬ እዚህ የተሰባሰብንበትም ዋነኛ ምክንያት የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ በህንድ አገር የሚገኘውን ቢ.ኤም.ቪ.ኤስ ኤስ ከሚባለው ድርጅት ጋር የሥራ ትስስር በመፍጠር በምስራቅ አትዮጵያ አጎራባች ክልሎች ውስጥ ለሚገኙ ከ270 እስከ 300 የአካል ጉዳተኞች ሰው ሰራሽ እግር ሰርቶ በመግጠም ለመንቀሳቀስ እንዲችሉ በማድረግ የአካል ጉዳተኛ ለሆኑ ወገኖቻችን እያደረገ ያለውን ድጋፍ ለማበረታት ነው ፡፡ ስለሆነም ይህ ጅምርና ተመሳሳይ የማህበረሰብ አገልግሎት ሥራዎች አጠናክሮ እንዲቀጥል ለሀረማያ ዩኒቨርሲቲ አደራ እላለሁ፡፡

መንግስት የተፈጥሮ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርት እንዲስፋፋ ለማድግ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ሐረማያ ዩኒቨርሲቲም በዚሁ የትኩረት አቅጣጫ መሠረት መንግስት ያስቀመጠውን ግብ ከማሳካት አኳያ አበረታች ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል፡፡ የዉጤቱ አንዱ ማሳያ የሆነውን የሐረማያ ቴክኖሎጂ እንስቲቲዪት መመረቁን በዚሁ እለት በይፋ አበስራለሁ፡፡

ክብራትና ክቡራን

በሀገራችን አንጋፋ ከሆኑት ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ የሆነው የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ገንዘብ ከፍለው ጠበቃ ማቆም ለማይችሉ ሴቶች፣ ህፃናት፣ አረጋዊያንና አካል ጉዳተኞች በየዓመቱ  እስከ 100 ሺህ ሰዎች ነፃ የህግ አገልግሎት በ43 ማዕከላት እና በሁለት የማህበረሰብ ተኮር የትምህርት ማዕከላት መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው በማድረግ፤ በአካባቢው የሚገኙ የጤና ተቋማትን የህክምና መስጫ ቁሳቁሶችን በማሟላት፤ በትምህርት ቤቶች የሚያስፈልጉ የትምህርት መረጃ ቁሳቁሶችን በማሟላት እንዲሁም በግብርና ፣ በስራ ፈጠራና ሌሎች ዘርፎች ጠንካራ ሥራዎችን በመስራት የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል፡፡

ዩኒቨርሲቲው የዕውቀት ማዕከል በመሆኑ በተለያዩ ዘርፎች ያሉ ዕውቀቶች የአካባቢውንና የሀገራችን ዜጎችን መጥቀምና በህይወታቸው ላይ ለውጥ እንዲመዘገብ የሚያስችል በመሆኑ የዛሬውን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲው ምሁራን እየቀረፁ በሚተገብሯቸው ፕሮጀክቶች ለወገኖቻችን የጎላ ጠቀሜታ ላስገኙ ምሁራን ምስጋናዬን እያቀረብኩ ለወደፊቱም በተጠናከረና ከአጎራባች ክልሎችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ያለው ዕውቀት የዜጎችን ህይወት ለመለወጥ እንዲችል የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የመንግስት ፍላጎት መሆኑን እየገለፅኩ መንግስትም የምታደርጉትን የጋራ የትብብር ሥራዎች የሚደግፍ መሆኑን ላረጋግጣላችሁ እወዳለሁ፡፡

ክቡራን የበዓሉ ታዳሚዎች

መንግስት ተግባራዊ እያደረገ የሚገኘው የዕድገትና ትራስፎርሜሽን ዕቅድ ሲጠናቀቅ በአሁኑ ወቅት ያሉብን ማህበራዊ ችግሮች ጎልቶ በሚታይ ደረጃ የሚቀረፉ በመሆናቸው ፤ይህን ዕውን ለማድረግ የሁሉን ኢትዮጵያዊ የጋራ ጥረት የሚጠይቅ በመሆኑ ባለን ዕውቀት፣ ሀብትና ጉልበት ተጠቅመን በርብርብ የሀገራችንን ሁለንተናዊ ዕድገት ዕውን እንድናደርግ በዚህ አጋጣሚ ጥሪዬን አቅርባለሁ፡፡

በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ህክምና ኮሌጅ ባልደረባ የሆኑት ህንዳዊ መምህር ፕሮፌሰር አር.ኤስ ባንሳል ከግብረሰናይ ድርጅቶች ጋር ባደረጉት ግንኙነት መሠረት ቀደም ሲል በትግራይ ክልል ለ400 አካል ጉዳተኞች እንዲሁም በአሁኑ ሰዓት በሀረሪ ክልል፣ በሶማሌ ክልል፣ በኦሮሚያ ክልል በምስራቅና ምዕራብ ሀረርጌ ዞኖችና እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስተደዳር ውስጥ ለሚገኙ ከ270 በላይ ወገኖቻችን ከህንድ ሀገር ድረስ መጥቶ የሰው ሰራሽ እግር በመስራት ድጋፍ ላደረገው ቢ.ኤም.ቪ.ኤስ.ኤስ እና የፋይናንስ ድጋፍ ላደረገለት የጄ.ኤም.ሲ ግብረሰናይ ድርጅቶች ምስጋናዬን እያቀረብኩ ለወደፊቱም ትብብራችሁ እንዳይለየን እጠይቃለሁ፡፡

በመጨረሻም በኢትዮጲያ የህንድ ኤምባሲ እና የኢትዮጲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጋራ በመሆን ይህንን በጎ አድራጎት ሥራ ለዜጎቻችን ስለአመቻቹልን በራሴና በኢትዮጲያ መንግስት ስም ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡

አመሰግናለሁ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

HTML tags are not allowed.