ሀረር  /ኢዜአ/ ታህሳስ 24/2008 የመልካም አስተዳደርና የሙስና ችግሮችን ማስወገድ ጸረ ሰላም ኃይሎች የሚፈጥሩትን ሁከትና እኩይ ተግባር በዘላቂነት መከላከል እንደሚያስችል የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች ገለጹ።

መምህራኑና የአስተዳደር ሠራተኞቹ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አካሂደዋል።

በውይይቱ ወቅት መምህራኑና  ሠራተኞቹ እንደገለጹት፣ የመልካም አስተዳደርና የሙስናች ግሮችን ማስወገድ አፍራሽ ኃይሎች የሚፈጥሩትን የሁከትና ብጥብጥ ተግባር በዘላቂነት ለመከላከል ያስችላል።

“መንግስት በተለይ የመልካም አስተዳደር ችግሮችና ብልሹ አሰራሮችን ለመቅረፍ አሁን የጀመረውን ስራ እስከ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ድረስ ወርዶ መስራትና ተግባሩንም በግልጽ ማሳየት ይገበዋል።” ብለዋል።

እንዲሁም ህብረተሰቡ የሚያቀርበውን ጥያቄ የመቀበልና መንግስት የሚያቅደውን የልማት ስራና ሌሎች ተግባራቶችን በየጊዜው ከህብረተሰቡ ጋር መወያየትና ህዝቡን ያማከለ ስራ ማከናወን ለችግሮቹ ቁልፍ መፍትሄ መሆኑን ጠቁመዋል።

ጥቂት ሕገወጥ ግለሰቦች ሆን ብለው ባልተጨበጠ መረጃ ህብረተሰቡን፣ ተማሪዎችንና ወጣቶችን ለማደናገርና ብጥብጥ እንዲነሳ በጠነሰሱት ሴራም ማዘናቸውን ገልጸዋል።

ድርጊቱ የሀገሪቱን ልማትና ሰላም የማይፈልጉቡ ድኖች አስተሳሰብ መሆኑን ያመለከቱት ተሳታፊዎቹ፣ እነዚህን የጥፋት ተላላኪዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።

በአፍራሽ ኃይሎች ተቀነባብሮ በተቋሙ የተፈጠረው ሁከት ፍጹም ከተማሪዎችና ከተቋሙ ማህበረሰብ ጋር ግንኙነት እንደሌለውና ተግባሩንም አጥብቀው እንደሚያወግዙ ገልጸዋል።

በውይይቱ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት አባልና የክልሉ መንገዶች ባለስልጣን ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ሙለታ እንደገለጹት፣ መንግስት ህዝቡ የሚያነሳቸውን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችና ችግሮች ደረጃ በደረጃ እየፈታነው።

ይህ በሆነበት ሁኔታ ጸረ ሰላም ኃይሎች በጠነሰሱት ሴራ የተነሳው ረብሻና የተፈጸመው ድርጊት ተቀባይነት የለውም።

በሀገሪቱ በተግባር በተረጋገጠው ዴሞክራሲዊ ስርአት መንግስት ማንኛውንም አይነት ጥያቄ ለማስተናገድ ምቹ ሁኔታፈጥሯል ያሉት አቶ ተስፋዬ፣ ጥቂት ግለሰቦች በሚነዙት የተዛባ አሉባልታ ወጣቶችና ተማሪዎች ሳይደናገሩ ጥያቄያቸውን ህጋዊ በሆነ መንገድ እንዲያቀርቡ አስገንዘበዋል።

የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጨመዳ ፊኒንሳ በበኩላቸው፣ በሀገሪቱ በተግባር የተረጋገጠው ዴሞክራሲዊ ስርአት ማንኛውንም አይነት ጥያቄ ለማስተናገድ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።

ተማሪዎች ሴረኞች በሚነዙት የተዛባ አሉባልታ መደናገር እንደ ሌለባቸውም አሳስበዋል።

መምህራንም ከመማር ማስተማሩ ስራ ጎን ለጎን ተማሪዎች ወደ አልተፈለገ አቅጣጫና እንዳያመሩ  የመምከር ስራን እንዲያከናውኑ ጠቁመዋል ሲል የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።