የሕይወት ፋና ስፔሻላይዝድ ቲችንግ ሆስፒታል ማስፋፊያ ስራ አበረታታች ደረጃ ላይ መሆኑ ተገለጸ

 

ሀረር ጥቅምት 8/2007 /የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት/ በሀረር ከተማ የሕይወት ፋና ስፔሻላይዝድ ቲችንግ ሆስፒታል የእናቶችና የህፃናት ጤና አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል እያከናወነ ያለው ስራ አበረታች መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ አስታወቁ።

ሆስፒታሉን ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፈዬን ጨምሮ የፌዴራልና የሐረሪ ክልል ከፍተኛ ሃላፊዎች  በጎበኙበት ወቅት የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶክተር ከሰተ ብርሃን አድማሱ እንደገለጹት የሕይወት ፋና ሆስፒታል ለሀረማያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች መማሪያና ለህብረተሰቡ የተሻሻለ የጤና አገልግሎት እንዲሰጥ ዩኒቨርስቲው ከክልሉ መንግስት ከተረከበበት ወቅት ጀምሮ የጤና አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል በማስፋፊያ ግንባታዎች ላይ እያሳየ ያለው ስራ አበርታች መሆኑን ገልጸዋል፡፡

hiwot fana hospital2

በተለይ ለምስራቅ ኢትዮጵያ አገልግሎት እንዲሰጥ አንድ ቢሊዮን በሚጠጋ ወጪ እየተገነባ የሚገኘው የሪፈራል ሆስፒታልና የመማሪያ ህንፃ  እየተፋጠነ በመሆኑ የሕክምና ባለሙያዎችና ቁሳቁስ በማሟላት ወደ ስራ ለመግባት ህንፃው በአጭር ጊዜ ሊጠናቀቅ እንደሚችል መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡

ለእናቶችና ለህፃናት ብቻ የጤና አገልግሎት የሚሰጠውና በሃምሳ ሚሊዮን ብር በCDC  ግንባታው የተጠናቀቀው ህንፃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ አስፈላጊው የሕክምና ቁሳቁስ ተሟልቶለት በአስቸኳይ ስራ እንዲጀምር አስገንዘበዋል፡፡

በተለይ በአሁኑ ወቅት ሆስፒታሎች የሕሙማንን ጭንቀት የሚያስወግዱ ንፁህና ፅዱ መሆን እንዳለባቸው ድሬዳዋ ከተማ ላይ ሰሞኑን በተካሄደው 16ኛው ዓመታዊ የጤና ዘርፍ ልማት መርሃ ግብር ውይይት ላይ ስምምነት የተደረሰ በመሆኑ ሆስፒታሉ ይህንን ተግባራዊ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬ ሆስፒታሉ በተለይ አዲስ እያስገነባ ያለው የሪፈራል ቲችንግ ህንፃ በካንሰር በሽታ ለሚሰቃዩ በርካታ ህሙማን የጨረር ሕክምና አገልግሎት ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል፡፡

hiwot fana hospital3

 

በተለይ አገልግሎቱ በጡትና ማህፀን ጫፍ ካንሰር በሽታ ለሚሰቃዩ እናቶች ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመው ግንባታው ከዚህ በበለጠ መፋጠን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የሐረማያ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ግርማ አመንቴ ሆስፒታሉ ለተማሪዎች መማሪያና ለማህበረሰቡ የተሻሻለ ጤና አገልግሎት እንዲሰጥ ዩኒቨርስቲው ከተረከበበት ጊዜ ጀምሮ የሚያከናውነውን የጤና አግልግሎት አሰጣጥ እያሻሻለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተለይ ለምስራቅ ኢትዮጵያ ሪፈራል ሆስፒታል ሆኖ የሚያገለግለው ህንፃ በስድስት ወራት ወስጥ እንደሚጠናቀቅ ጠቁመው ስራው ሲጠናቀቅ ተኝተው ለሚታከሙ ህሙማን ዘጠኝ መቶ አልጋ ያለውና ለጤና ተማሪዎችም ከፍተኛ የትምህርት መስጫ ተቋም ሆኖ እንደሚያገለግል ገልፀዋል፡፡

የሐረሪ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሙራድ አብዱልሃዲ ሆስፒታሉ ለክልሉና ለአካባቢው ማህበረሰብ ለሰባ ዓመታት በላይ የጤና አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

የሐረማያ ዩንቨርስቲ ሆስፒታሉን ከተረከበ ነሀሴ 22/2002 ዓ.ም ጀምሮ የጤና አገልግሎትና የማስፋፊያ ግንባታ እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመው በተለይ የሪፈራል ህንፃው ግንባታ ተጠናቆ ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጥ በሚያደርገው ጥረት የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡

ቀዳማዊት እመቤት ሮማን  ተስፋዬን  ጨምሮ የፌደራል እና የክልሉ ባለስልጣናት የሆስፒታሉን የጤና አገልግሎት አሰጣጥና አንድ ቢሊዮን በሚጠጋ ወጪ እየተገነባ ያለውን ሪፈራል ሆስፒታልና በሐረሪ ክልል ስር የሚገኘውን የጀጉል ሆስፒታልን ጎብኝተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

HTML tags are not allowed.