የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ 15 አዲስ የትምህርት ፕሮግራም ሊጀምር ነው

 

ሐረር /ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት/ መስከረም 28/2007 የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በያዝነው የትምህርት ዘመን 15 አዲስ የትምህርት ፕሮግራሞች ለመጀመር የሚያስችለውን ዝግጅት ማጠናቀቁን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት አስታወቁ፡፡
ዩኒቨርሲቲው ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ የተማሪዎች የመቀበል አቅሙን 30 በመቶ ማሳደግ መቻሉም ተገልጿል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ግርማ አመንቴ ትናንት እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው በ2007 የትምህርት ዘመን የሚጀምራቸው አዲስ የትምህርት ፕሮግራሞች በዶክትሬት፣በሁለተኛና መጀመሪያ ዲግሪ የሚሰጡ የትምህርት ዓይነቶች ናቸው።
ከፕሮግራሞቹ መካከል ሁለቱ በዶክትሬት ፣ስምንቱ በሁለተኛ ዲግሪና ቀሪዎቹ ሶስት አዳዲስና ቀደም ሲል ሲሰጡ የነበሩና ሌሎቹ ደግሞ ጥናትና ክለሳ ተደርጎባቸው ካሪኩለም ተቀርጾላቸው የጸደቁ የትምህርት ዓይነቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከሚጀምራቸው አዳዲስ የትምህርት ፕሮግራሞች መካከል በዶክትሬት ዲግሪ ማይክሮ ባይሎጂና ሬንጅ ኢኮሎጂ እና ድራይ ላንድ ባዮዳይቨርሲቲ እንዲሁም በሁለተኛ ዲግሪ በሶሻል ሳይኮሎጂ፣በካሪኩለም ጥናት፣በልዩ ፍላጎት ትምህርት፣በአለም አቀፍ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ህግ፣በስፖርት ህክምና፣በኢነርጂ ፣ኢኮኖሚክስና ሌሎች የትምህርት ዘርፎች እንደሚገኙበት ገልጸዋል።
በቅድመ ምረቃ በሸንኮራ አገዳ ልማት፣በውሃ መስኖና ውሃ አቅርቦት፣የአካባቢ ጥበቃ ምህንድስና ትምህርቶች እንደሚገኙባቸው ጠቁመው ፕሮግራሞቹን ለመጀመር ብቁ መምህራን መኖራቸውን ገልፀዋል።
ዩኒቨርሲቲው በያዝነው የትምህርት ዘመን አራት ሺህ 650 አዲስ ተማሪዎችን መቀበሉን ገልጸው ይህም ዩኒቨርሲቲው በ2004 የትምህርት ዘመን ከተቀበላቸው ሶስት ሺህ 500 አዲስ ተማሪዎች ዘንድሮ 30 በመቶ ማሳደግ መቻሉን አስታውቀዋል።
ዩኒቨርሲቲው በዋናው ግቢ ሐረርና ጭሮ ከተማ በሚገኙ የጤናና ግብርና ኮሌጆች የሚገነቡት የመማሪያ፣የመመገቢያና የተለያዩ ህንጻዎች ሲጠናቀቁ ስድስት ሺህ አዲስ ተማሪዎችን እንደሚቀበል ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከማስተማር ስራው በተጓዳኝ ችግር ፈቺና ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ የምርምር ስራዎችን በማከናወን የማህበረሰብ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን አስታውቀዋል።
በሽታና ድርቅን በመቋቋም የተሻለ ምርት የሚሰጡ የበቆሎ፣ማሽላ፣ቦሎቄ፣ድንች ዝርያዎችን ለምዕራብና ምስራቅ ሐረርጌ ዞን አርሶ አደሮች ማሰራጨቱን ገልጸዋል።
የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በ2006 የትምህርት ዘመን ከ34 ሺህ የሚበልጡ ተማሪዎችን በዶክትሬት፣በሁለተኛና በመጀመሪያ ዲግሪ በመደበኛ፣ በተከታታይ፣በርቀትና በክረምት ማስተማሩ መገለጹ ይታወሳል።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

HTML tags are not allowed.