የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የቲማቲም ምርትን በእጥፍ ለማሳደግ ምርምር እያካሄደ ነው

 

Ethiopian News Agency/ሀረር ሚያዝያ 24/2006

በምስራቁ የሐገሪቱ ክፍል በአነስተኛ ደረጃ እየተመረተ የሚገኘውን የቲማቲም ምርት በእጥፍ ለማሳደግ የጀመረው ምርምር ውጤት ማሳየቱን የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።
ዩኒቨርሲቲውና በቲማትም ምርት ማሻሻያ ላይ እያከናወነ ያለውን የምርምር ቴክኖሎጂ ትናንት ለግብርና ባለሞያዎች፣ለተመራማሪዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት አስጎብኝቷል።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎትና ኢንተርፕራይዝ ልማት ምክትል ፕሬዜዳንት ፕሮፌሰር ከበደ ወልደጻዲቅ በጉብኝቱ ወቅት እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው የቲማቲም ምርምር ቴክኖሎጂ እያከናወነ ያለው በእስራኤል ከሚገኘውና ለትርፍ ካልቆመው ፌር ፕላኔት የተባለ ድርጅት ጋር ነው።
በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ እያከናወነ ያለው ምርምር ውርጭና በሽታን በመቋቋም ከፍተኛ ምርት በሚሰጡ 30 የቲማቲም ዝርያዎች ላይ መሆኑን ጠቁመው ዝርያዎቹ በአንድ የቲማቲም ተክል ላይ እስከ ሶስት ኪሎ ግራም ምርት በመስጠት ከሀገር ውስጥ ከሚገኙ ዝርያዎች ምርቱ በእጥፍ ብልጫ ማሳየቱን አስታውቀዋል።
ቴክኖሎጂው የአካባቢው አርሶ አደሮች በማሳቸው ከሚያመርቱት ሰብል ገቢ ያልተናነሰ ውጤት የሚሰጥና ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድግ መሆኑን ተናግረዋል።

የምርምር ቴክኖሎጂ ከሚካሄድባቸው የቲማቲም ዝርያዎች መካከል ሶስቱን ዝርያዎች በሚቀጥለው ዓመት ለአካባቢው አርሶ አደሮች የማስተዋወቅና ዝርያዎቹን የማሰራጨት ስራ እንደሚካሄድ ገልጸዋል።
የፌር ፕላኔት መስራችና ዋና ስራአስኪያጅ ዶክተር ሾዋስዋን ሀረን ድርጅቱ በውጭ ሀገር ከሚገኝ ምርጥ ዘር አቅራቢ ድርጅት ውርጭና በሽታን ተቋቁመው ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ የቲማቲም ዝርያዎችን ወደ ኢትዮዽያ በማስገባት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በመስራት ላይ ነው።
ድርጅቱ በቡታጅራ አካባቢ ባከናወነው የመጀመሪያ የቴክኖሎጂ ስራ ዝርያው በሄክታር ከ600 እስከ 850 ኩንታል ምርት መስጠቱን ገልጸው ይህም በአካባቢው ከሚገኙት ዝርያዎች በእጥፍ ብልጫ ማሳየቱን አስታውቀዋል።
በምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል ዝርያዎቹን ለማስፋፋትና የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በዩኒቨርሲቲው መሬት ላይ በተከናወነው የምርምር ስራ ውጤቱ ተመሳሳይ ሆኖ መገኘቱን ገልጸዋል።

ከምዕራብና ምስራቅ ሐረርጌ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት የመስኖ ባለሞያ አቶ ኤፍሬም ግርማና አቶ ዩስፍ ሱፊ ዝርያዎቹ ውርጭንና በሽታን ተቋቁመው ከፍተኛ ምርት መስጠታቸው በአካባቢው ውስን የሆነውን የቲማቲም ምርት ለማሳደግ ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው ብለዋል።
ምርቱ ከተሰበሰበ በኃላም ለብዙ ቀናት ሳይበላሽ መቆየቱና ብዙ መሬት ሳይወስድ በአነስተኛ መሬት ላይ ከፍተኛ ምርት መስጠቱ ለአካባቢው አርሶ አደር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንሰደሚሰጥ ተናግረዋል።
በጉብኝቱ ወቅት የግብርና ባለሞያዎችና ተመራማሪ ምሁራን፣ከመንግስትና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅት የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
ከምርምር ቴክኖሎጂው በተጨማሪ በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ፣በመስኖ ልማትና በሌሎች ርዕሶች ላይ ከእስራል ሀገር በመጡ ምህራን ልምድና የተሞክሮ ልውውጥ ተካሂዷል።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

HTML tags are not allowed.