የዩኒቨርሲቲው መምህራና የአስተዳደር ሰራተኞች በሀገራዊ ጉዳይ፣ በዩኒቨርሲቲው በ2008 የስራ አፈጻጸምና በ2009 እቅድ ላይ ትናንት ውይይት ማካሄድ ጀምረዋል። ውይይቱ በዋናው ግቢ በሁለት መድረኮችእን በሀረር ካንፓስም በተመሳሳይ ሁለት መድረኮች ተከፋፍሎ እየተካሄደ ይገኛል፡፡በመክፈቻው ዕለት የኢፌዲሪ የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ልማት ተቋም ዋና ዳይሬክተር አቶ ደኤሳ ለታ በሃያ አምስት ዓመታት ጉዞ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ሚናና ለቀጣይ ተልዕኮ የሚገባው አቅጣጫ የሚለውን ጽሁፍ ለተሳታፊው አቅርበዋል።
ዕሁፉም በሩብ ምዕተ ዓመታት በከፍተኛ ትምህርት ተቋም የተመዘገቡ ውጤቶችና የልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት አገራዊ ስኬቶች፣ለኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ግንባታና ለህዳሴ ጉዞ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ሊኖረው የሚገቡ ስራዎችና የባለድርሻ አስተዋጽ የሚሉትን በዝርዝር አቅርበዋል።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጨመዳ ፊኒንሳ ውይይቱን ሲከፍቱ ባደረጉት ንግግር ዩኒቨርሲቲው የትምህርት ተደራሽነትን በማሳደግ በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና በዶክትሬት ድግሪ ብቃት ያለው የሰለጠነ የሰው ሃይል ለዘመናት እያፈራ ይገኛል።ፍላጎትን መሰረት ያደረገና ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በማከናወን ምርትና ምርታማነት የማሳደግና የማህበረሰብ አገልግሎት ለአርሶ አደሩና ለማህበረሰቡ በመስጠት መጠነ ሰፊ ስራም እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።በ2008 የትምህርት ዘመን በተቋሙ ውስጥ የተፈጠሩትን ሁከትና ብጥብጥ የዩኒቨርሲቲው መምህራንና ሰራተኞቸ እርስ በርስ፣ ከአካባቢው ማህበረሰብና አስተዳደር አካላት ጋር በመተባበር ሁኔታውን በማረጋጋትና የመማር ማስተማሩ ስራ ሳይሰተጓጎል እንዲቀጥል ከፍተኛ አስተዋጽዎ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው የሚያከናውነው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ፣የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎችን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አካላት እያከናወኑት የሚገኘውን አስተዋጽዎም በቀጣይም ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የውይይቱና የስልጠናው ዋና ዓላማ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ለአገር ልማት እያበረከተ የሚገኘውን አስተዋጽዎና ክፍተቶችን በመለየት ዴሞክራሲያዊ አንድነት ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር፣ የትምህርት ጥራትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን ለመፈጸም የሰራዊት ግንባታ ሚናና የተቋሙ የ2008 የስራ አፈጻጸምና የ2009 የስራ እቅድን በጋራ ለመገምገም መዘጋጀቱንም አመልክተዋል።

የሐረሪ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሐምዛ መሀመድ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የተጣለበትን የመማር ማስተማር፣የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎችን ለማረጋገጥ የመምህራኑና የአስተዳደር ሰራተኛው ሚና የጎላ ነው።

ይህንንም ተልዕኮ ለማሳካት በተቋሙ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራ መጎልበት ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው መምህራኑና የአስተዳደር ሰራተኛው ከዚህ ቀደም የነበሩ ክፍተቶችን በመለየትና መልካም ተሞክሮዎችን በማጎልበት የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽዎ ማበርከት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።በዩኒቨርሲቲው ዋናው ግቢና በሐረር ከተማ በሚገኘው የጤናና የህክምናና ሳይንስ ኮሌጅ ለተከታታይ 8 ቀናት በሚካሄው ውይይትና ስልጠና 5 ሺ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች የተሳተፉ ሲሆን በቆይታቸውም በሃያ አምስት ዓመታት ጉዞ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ሚናና የቀጣይ ተልዕኮ፣ በአገሪቱ አንድ የጋራ ማህበረሰብ የመገንባት አስፈላጊነት፣ የሰራዊት ግንባታ ስራና የትምህርት ጥራት በከፍተኛ ትምህርት ተቋምና የዩኒቨርሲቲው የ2008 የስራ አፈጻጸምና የ2009 የስራ እቅድ ላይ በቡድንና በጋራ ውይይት ያደርጋሉ።