የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በሳይንስ ትምህርት ዘርፎች ለ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የማጠናከሪያ የክረምት ትምህርት ሰጠ

 

ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በአካባቢው የሚገኙ የመለስተኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሳይንስ ተማሪዎች ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ያላቸው ዝንባሌ እንዲጎለብት እና ክህሎታቸው እንዲዳብር በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች በየዓመቱ በክረምት የእረፍት ጊዜ በዩኒቨርሲቲው መምህራን የማጠናከሪያ ትምህርት ይሰጣል፡፡
ዘንድሮ ለአምስተኛ ጊዜ ከሐረሪ ክልል ፣ ከምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ ዞኖች ትምህርት ቤቶች ለተውጣጡ 380 ተማሪዎች ከሐምሌ 12 እስከ ነሐሴ 21 ቀን 2008 ዓ/ም በዩኒቨርሲቲው ጊቢ ውስጥ በሳይንስና ቴክኖሎጂ የትምህርት ዘርፎች በፊዚክስ ፣ ሂሳብ ፣ ኬሚስትሪ ፤ ባዮሎጂና በኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ ትምህርቶች ላይ በተግባር የታገዘ ትምህርት ተሰጥቷል፡፡
1

በስልጠናው ላይ የተካፈሉ ተማሪዎች እንዳሉት በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በነበራቸው ቆይታ ከዋና ዋና የሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርቶች በተጨማሪ የእንግሊዘኛ ቋንቋና የአካል ብቃት ማጎልመሻ ስልጠና እንደተሰጣቸውና የእረፍት ጊዜያቸውንም ለቀጣይ ዓመት ትምህርት በቂ ዝግጅት እያደረጉ ለማሳለፍ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል፡፡
2

ከካራሚሌ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመጣችው የ8ኛ ክፍል ተማሪ ሜሮን ሰለሞን የተሰጠውን ትምህርት አስመልክታ እንደተናገረችው በትምህርት ቤታቸው ውስጥ ቤተ-ሙከራ ባለመኖሩ እንደ ፊዚክስ ፣ ኬሚስትሪና ባዮሎጂ ያሉ ትምህርቶችን የተግባር ልምምድ ሳያደርጉ እንደሚማሩ አስታውሳ አሁን ደግሞ ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በራሱ መምህራንና ላብራቶሪ ውስጥ ልምምድ እያደረጉ እንዲማሩ ማድረጉ በሀሳብ ደረጃ የሚያውቁትን በሙከራ አግዘው የተሟላ ግንዛቤ እንዲጨብጡ እንዳደረገ ተናግራለች ፡፡
3

በምስራቅ ሀረርጌ ዞን የደደር 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ10 ክፍል ተማሪ የሆነችው ኢክራም ረመዳን የተሰጣቸው የማጠናከሪያ ትምህርት በሳይንስ ትምህርቶች ላይ ያላቸውን ፍላጎት ያሳደገላቸውና ጥሩ የውድድር ስሜትንም ያሳደረባቸው እንደነበር ተናግራለች፡፡
4

ከሐረሪ ክልል የመጣው ተማሪ አብዱሰመድ መሀመድ ደግሞ የዩኒቨርሲቲ ህይወትን በተመለከተ ሲያስጨንቁት ለነበሩ ጥያቄዎች ምላሽ ያገኘበትና ጥሩ ዕውቀት የቀሰመበት ቆይታ እንደነበረው ተናግሯል፡፡
ሌላው ከሐረሪ ክልል የመጣው የ10ኛ ክፍል ተማሪ ፈቲህ ረመዳን በበኩሉ የሚማሯቸውን የሳይንስ ትምህርቶች በተመለከተ በላብራቶሪ የተደገፈ ትምህርት እንደተሰጣቸውና ይህንንም ትምህርት ማግኘታቸው በተሟላ ላብራቶሪ ውስጥ በባለሞያ እየታገዙ ኤክስፐርመንት የመስራት እድል እንደፈጠራላቸውና ለምርምር ያላቸው ፍላጎትም እንዲጨምር እንዳደረገ ገልጿል፡፡ ተማሪ ፈቲ በአጠቃላይ በዩኒቨርሲቲው በነበረው ቆይታ በትምህርት ካገኘው ዕውቀት በተጨማሪ የዩኒቨርሲቲ ህይወት ምን እንደሚመስል በማየትና ልምድ በመውሰድ ጥሩ ጊዜ እንዳሳለፈ እና ለዚህም ዩኒቨርሲቲውን ማመስገን እንደሚፈልግ ተናግሯል ፡፡
6
በሳይንስና ስነቀመር ኮሌጅ መምህርና የስልጠናው አስተባባሪና የሆኑት መምህር ኦቦማ ነጋሳ እንደገለጹት ተማሪዎች በክፍል ውስጥ የሚማሩትን ትምህርት በቤተ ሙከራ እየተገበሩ የተሟላ ዕውቀት ለመጨበጥ በትምህርት ቤቶች ውስጥ የተሟላ ቤተሙከራ አለመኖሩ ትልቅ ክፍተት እንደሆነ ጠቅሰው ሐረማያ ዩኒቨርሲቲም ይህንን ችግር ለመቅረፍ እንዲያስችል ከትምህርት ቤቶች ጋር በመተባበር አስፈላጊውን ወጪ በመሸፈን ተማሪዎችን ወደ ዩኒቨርሲቲው በማምጣት በተሟሉ የፊዚክስ ፣ የኬሚስትሪና የባዮሎጂ ላብራቶሪዎች ውስጥ ልምድ ባላቸው መምህራን ስልጠና እንዲያገኙ ማድረጉን ገልጸዋል ፡፡
7
ኦቦማ ነጋሳ አያይዘው እንዳሉትም ዩኒቨርሲቲው ለተማሪዎች ከሚሰጠው የማጠናከሪያ ትምህርት በተጨማሪ በተመሳሳይ መልኩ ከትምህርት ቤቶች ለተወጣጡ መምህራን በበጋው ወቅት የአቅም ግንባታ ስልጠና በዩኒቨርሲቲው ባለሞያዎች እንደተሰጠ አስታውሰው ይህም በአገር ደረጃ በሳይንስና ቴክኖሎጂ የላቀ ክህሎት ያላቸው ተማሪዎችን ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርቶች ላይ በማተኮር ለአንድ ወር የተሰጠውን ትምህርት የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ተኮር ልማት ዳይሬክቶሬት ከተፈጥሮና ስነ-ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ እንዲሁም ከትምህርት ቢሮዎች ጋር በመተባበር ያካሄዱት ሲሆን በአጠቃላይ ከተሳተፉ 380 ተማሪዎች መካከል ሰላሳ በመቶ የሚሆኑት ሴቶች እንደሆኑና በቀጣይ ዓመትም ትምህርቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡
8
የማጠናከሪያ ት/ት የተሰጣቸው ተማሪዎች በከፊል

Leave a Reply

Your email address will not be published.

HTML tags are not allowed.