የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አባላት በሀገሪቱ እቅድ ላይ ውይይት ጀመሩ

 

ሀረር መስከረም 5/2008 በመጀመሪያው የእድገትና ትራንሰፎርሜሽን እቅድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ከማስፋፋት ጎን ለጎን ለትምህርት ጥራት መጠበቅና የሰለጠነ የሰው ሀይል በማፍራት በኩል አበረታች ስራ መከናወኑን የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አስታወቁ። የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች በአንደኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አፈጻጸምና በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይ ዛሬ ውይይት ጀምረዋል። የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዜዳንትና የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አብዱላዚዝ መሐመድ እንደገለጹት ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ የሰላም፣የልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታን ለማጎልበት ሰፊ ርብርብ በማድረግ ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቧል።በተለይ በመጀመሪያው የአምስት ዓመት የእድገትና ትራንሰፎርሜሽን እቅድ ዘመን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ከማስፋፋት ስራ ጎን ለጎን የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅና የሰለጠነ የሰው ሀይል ለበማፍራት አበረታች ስራ መከናወኑን ተናግረዋል።

በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ትልቁ የትኩረት አቅጣጫ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ የሚደረገው ጉዞ መሆኑን መንግስት በእቅዱ ማረጋገጡን አስታውቀዋል።እቅዱን ስኬታማ ለማድረግ በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራን በማስፈን ብቁና የሰለጠነ የሰው ሀይል የማፍራት ስራ፣ የትምህርት ጥራትን ማጎልበትና ኢንዱስትሪና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን በጥናትና ምርምር የማስተሳሰር ስራ ትኩረት የሚሰጠው እንደሆነ የስልጠናው ዋና ዓላማ መሆኑን ገልጸዋል። የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የስትራቴጂካዊ አመራርና ተቋማዊ ለውጥ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አበበ በላቸው በመጀመሪያው የእድገትና ትራንሰፎርሜሽን እቅድ በግብርና፣በትምህርት፣በጤና፣በመሰረተ ልማት ግንባታ፣በኢንዱስትሪና ሌሎች ዘርፎች የተከናወኑ ስራዎችን በጽሁፍ አቅርበዋል።

የትምህርት ሽፋንን ለማሳደግም በ2002 መጨረሻ 82 በመቶ የነበረውን የአንደኛ ደረጃ ንጥር የትምህርት ተሳትፎ ወደ 92 በመቶ ፣37 ነጥብ 9 በመቶ የነበረውን የሁለተኛ ደረጃ የትምህርት ተሳትፎ ወደ 62 በመቶ ከፍ ማድረግ እንደተቻለ ገልጸዋል። በቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠናና የቅበላ አቅምን የማሳደግ ስራ ከመከናወኑ በተጨማሪ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የማስፋፋት፣በቅድመ ምረቃ የቅበላ አቅምን 400 ሺህ፣በድህረ ምረቃ ደግሞ የቅበላ አቅምን ወደ 28 ሺህ ማሳደግ መቻሉን አስታውቀዋል፡፡ከከፍተኛ ትምህርት አግባብነት አንፃር 70 በመቶ ተማሪዎች በሳይንስና ኢንጂነሪንግ፣ ከነዚህም መካከል 40 በመቶው በኢንጅነሪንግ መስክ እየተማሩ መሆናቸው ገልጸዋል።

መሰረታዊ የጤና አገልግሎትን ለሁሉም ዜጋ ለማዳረስ በሀገሪቱ ሁሉም አካባቢ ጤና ጣቢያና ጤና ኬላ በመገንባት መሠረታዊ የጤና አገልግሎት የሚሰጡ 40 ሺህ የጤና ኤክስቴንሽንና መካከለኛና ከፍተኛ የጤና ባለሙያዎችን በስፋት በማሰልጠን ወደ ሥራ እንዲሰማሩ መደረጉን ገልጸዋል።በመሰረተ ልማት የአስፓልትና ገጠር መንገድ፣የባቡር፣የቴሌኮሙዩንኬሽን፣ንጹህ የመጠጥ ውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ግንባታ፣በኢንዱስትሪ ልማት በተለይ በጥቃቅንና አነስተኛ ተቋም ልማት፣ቁጠባና ኢንቨስትመንትን የማጠናከር ስራዎች እንደሚገኙበት በጽሁፋቸው አቅርበዋል።በአንደኛው የእድገትና ትራንሰፎርሜሽን እቅድ በህዝቡ ዘንድ የባለቤትነት ስሜት የታየበት፣ከፍተኛ የልማት መነሳሳት የተፈጠረበትና አመርቂ ውጤት የተመዘገበበት መሆኑን አቶ አበበ ገልጸዋል።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዜዳንት ፕሮፌሰር ጨመዳ ፊኒንሳ ውይይቱ በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የተገኙ ስኬቶችን ለማጎልበትና ያጋጠሙ ችግሮችን በማስወገድ ለቀጣዩ እቅድ በቂ ዝግጅት እንድናደርግ ያግዛል ብለዋል።ውይይቱ በእቅድ ዘመኑ ለትምህርት ጥራት መጓደል ምክንያት የሆኑ ችግሮችን የመለየት፣በተቋማዊ ለውጥ ትግበራና በትምህርት የልማት ሰራዊት ግንባታ ፣ በመልካም አስተዳደር ስራ ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን በማስወገድ የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚረዳም ተናግረዋል።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኛች በሰጡት አስተያየት በመጀመሪያው እቅድ አፈጻጸም ላይ የመልካም አስተዳደርና ኪራይ ሰብሳቢ ችግሮችን የመለየትና የተወሰዱ እርምጃዎች በግልጽ ያለመቀመጥ፣በግል ኮሌጆች ላይ የሚታየው የትምህርት ጥራት ጉድለትን መንግስት እየተመለከተ አይደለም ብለዋል።አዲስ በተከፈቱ የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የትምህርት መስጫ ቁሳቁስ አለመሟላትና የንድፈ ሃሳብ ትምህርት ላይ ብቻ ማተኮር፣ የሁለተኛና 3ኛ ዲግሪ ትምህርት እጥረት፣ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ላይ የትምህርት ጥራት ጉድለት መኖሩን ተናግረዋል።በታክስ አሰባሰብ፣ አርሶ አደሩን ከዝናብ ጥገኝነት ያለማላቀቅ ሁኔታ መታየት፣ የኤሌትሪክ መብራት መቆራረጥ እና ችግሮችን ሊፈታ የሚችል የመልካም አስተዳደር እጦትና ሌሎችም ችግሮች በሀገሪቱ እንደሚታይ ገልጸዋል።

ከመምህራኑና አስተዳደር ሰራተኞቹ የተሰነዘሩት አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተገቢና ትክክለኛ በመሆናቸው በሂደት እየታዩ የሚፈቱ መሆናቸውን የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድርና የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አብዱላዚዝ መሐመድ እና የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጨመዳ ፊኒንሳ ገልጸዋል።  


በዩኒቨርሲቲው ዋና ግቢና ሐረርና ጭሮ ከተማ በሚገኙ ኮሌጆች ዛሬን ጨምሮ ለሰባት ቀናት በሚካሄደው ውይይት ሁሉም መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች  በመሳተፍ በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አፈጻጸምና በሁለተኛው የትራንስፎርሜሽን እቅድ፣ በትምህርት ጥራት ላይ የባለድርሻ አካላት፣የአመራር ሚናና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ በሚሉና በሌሎችም ርዕሶች ላይ ውይይት ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።

በውይይቱ መክፈቻ ቀን ትኩረት የተደረገው በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በተገኙ የልማት ውጤቶችና ባጋጠሙ ችግሮች ላይ ነው። 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

HTML tags are not allowed.