የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ለዶ/ር ጣማዶ ጣና የሙሉ ፕሮፌሰርነት አካዳሚክ ማዕረግ ሰጠ፡፡

 

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ቦርድ ትናንት ባካሄደው ስብሰባ ለዶ/ር ጣማዶ ጣና በአግሮኖሚ የሙሉ ፕሮፌሰርነት አካዳሚክ ማዕረግ ሰጠ፡፡

ዶ/ር ጣማዶ ጣና በደቡብ ክልል በወላይታ ዞን በ1960 ዓ.ም የተወለዱ ሲሆን የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸዉን በወላይታ ሶዶ አጠቃላይ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተከታትለዋል፡፡ የባችለር ዲግሪያቸዉን በዕጽዋት ሳይንስ እና የማስተርስ ዲግሪያቸዉን በአግሮኖሚ ከሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ያገኙ ሲሆን የዶክተሬት ዲግሪያቸዉን በአግሮኖሚ ከሲዊድን ግብርና ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡

ዶ/ር ጣማዶ ጣና በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነትና በተመራማሪነት ለ25 ዓመታት ያህል አገልግለዋል፡፡ በነዚህ ጊዜያት 12 የተለያዩ ኮርሶችን ለባችለር፣ ለማሰተርስ እና ለዶክተሬት ፕሮግራሞች በከፍተኛ ብቃት ያስተማሩ ሲሆን 5 የማስተማሪያ ፅሁፎችን ያዘጋጁ ሲሆን 122 የማሰተርስ እና 14 የዶክተሬት ተማሪዎችን በብቃት አማክረዉ አስመርቀዋል፡፡

በምርምር ሥራቸዉም በለዉዝ፣ በእንሰት፣ በወራሪ መጤ አረሞችና ወዘተ በአገራዊና ከአገር ዉጭ ባሉ ድርጅቶች ገንዘብ የተደገፉ በርካታ የምርምር ፕሮጄክቶችን በመሥራት የምርምር ዉጤቶችን በራሳቸዉና ከምርምር ባልደረቦቻቸዉ ጋር በመሆን 60   የምርምር ጽሁፎችን በታወቁ ዓለም አቀፍና አገራዊ ጆርናሎች ያሳተሙ ሲሆን በበርካታ ዓለም አቀፍና አገራዊ ኮንፍራንሶች ተሳትፈዉ የምርምር ጽሁፎችን አቅርበዋል፡፡

በማህረሰብ አገልግሎት ዘርፍም የምርምር ዉጤቶች ለተጠቃሚዎች እንዲደርሱ በርካታ ሥልጠናዎችንና የማማከር አገልግሎት መንግሥታዊና መንግሥታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች፣ ለግብርና ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች የሰጡ ሲሆን በበርካታ አገራዊ ኮሚቴዎች በመሳተፍ በሙያቸዉ አስፈላጊዉን አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡

ከዚህም በተጨማር ዶ/ር ጣማዶ ጣና የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ፕሮግራሞች ቢሮ ኃላፊ እና የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ መሥራች ፕሬዚዳንት በመሆን አገልግለዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

HTML tags are not allowed.