ዜና ዕረፍት

 

ታዋቂው ተመራማሪ ፕሮፌሰር ተካልኝ ማሞ ባደረባቸው ህመም ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡
1
በተማሪነት በ1966 ዓ.ም ዩኒቨርሲቲያችንን የተቀላቀሉት ፕ/ር ተካልኝ ማሞ በዩኒቨርሲቲያችን ውስጥ በመምህርነት ፣ በተመራማሪነት ፣ በደብረ ዘይት እርሻ ምርምር ማዕከል ዳይሬክተርነት ፣ በአስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዝዳንትነት በርካታ የኤም.ኤሲ እና ፒ.ኤች.ዲ ተማሪዎችን በማማከር ሳይንሳዊ ጽሑፎችን አበርክተዋል፡፡ ከዩኒቨርሲቲያችን ከለቀቁ በኋላ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የዩኒቨርሲቲያችን ስራ አመራር ቦርድ አባል በመሆንም አገልግለዋል፡፡
በ1996 ዓ.ም በግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታነት ተሹመው ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር ካገለገሉ በኋላ ለህክምና ወደ ውጪ ሀገር በመሄድ ህክምናቸውን ተከታትለው ሲመለሱም በጠቅላይ ሚኒስቴር ፅ/ቤት በሚኒስትር ዲኤታነት እንዲሁም የምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴሩ አማካሪነት በመሆን ከአምስት ዓመት በላይ አገልግለዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስቴር ፅ/ቤት የፖሊሲ ጉዳይ አማካሪ ሆነው ባገለገሉባቸው ጊዜያት በአሁኑ ወቅት በመተግበር ላይ የሚገኘውን የማህበረሰብ አቀፍ ተፋሰስ ልማት ስትራቴጂ (Community-Based Participatory Water-Shed Development) በመንደፍና በዘርፉ ላይ የሚሰሩ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ረቂቅ ፖሊሲውን አዘጋጅተዋል፡፡ በሀገራችን የሚገኝ አሲዳማ አፈር በኖራ በማከም ለግብርና ስራ አመቺ እንዲሆን ቴክኖሎጂውን አመንጭቶ የማስተዋወቅ፣ የኮትቻ አፈር በሚገኝባቸው አካባቢዎችም አፈሩን የማንጠፍጠፍ ቴክኖሎጂን በማስተዋወቅ እንዲሁም በሀገራችን የተጎሳቆሉ የተፈጥሮ ሀብቶች እንዲያገግሙ የሚያስችሉ አሰራሮችን በመንደፍና በማስተዋወቅ የሀገራችን ግብርና ውጤት እንዲሻሻል ፕሮፌሰር ተካልኝ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ተጨባጭ ለውጥ እንዲታይ ሙያዊ አስተዋፅዖዋቸውን አበርክተዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር የሀገራችን የአምስት ዓመት የአፈር ለምነት ፍኖተ ካርታን በ2003 ዓ.ም በማዘጋጀት ከአንደኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ጋር ተጣጥሞ ተግባራዊ እንዲደረግ አድርገዋል፡፡
ፕሮፌሰር ተካልኝ ማሞ በሀገራችን አንቱ የተባሉ የአፈር ሳይንስ ተመራማሪ የነበሩ ሲሆን በሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ እውቅናና ሽልማቶችንም አግኝተዋል፡፡ ከነዚህም መካከል እ.ኤ.አ በያራ የ2014 የአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት ሎሬት ተብለው ሲሸለሙ በ2015 የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት ዓለም ዓቀፍ ልዩ የአፈር አምባሳደሮች ብሎ ሁለት ተመራማሪዎችን ሲመርጥ ፕ/ር ተካልኝ አንደኛው ተመራጭ ነበሩ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እ.ኤ.አ በ2016 ዓለም አቀፍ የማዳበሪያ አምራቾች ማህበር ከ30 ዓመት በላይ የኢትዮጵያን አፈርና የተፈጥሮ ሀብትን ለመጠበቅ ባደረጓቸው ምርምሮች 11 ሚሊየን አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ በማድረጋቸው ማህበሩ የሚያዘጋጀውን የኖርማን ቦርላግ ሽልማት ተሸላሚ የሆኑበት ከብዙዎቹ ሽልማቶቻቸው ለአብነት የሚቀርቡ ናቸው፡፡
ፕ/ር ተካልኝ ማሞ በቅርቡ በሞሮኮ በሚገኘው የአፍሪካ አፈር ጥናት ማዕከል ኃላፊ ሆነው በማገልገል ላይ የነበሩ ሲሆን ባደረባቸውን ህመም ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ አስከሬናቸውም ዓርብ ጷጉሜ 3 ቀን 2009 ዓ.ም ወደ ሀገር ውስጥ ገብቶ ስርዓተ ቀብራቸው ቅዳሜ ጷጉሜ 4 ቀን 2009 ዓ.ም በአዲስ አበባ መንበረ ፀባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ይፈጽማል፡፡
የሀረማያ ዩኒቨርሲቲም ለቤተሰቦቻቸው፣ ለስራ ባልደረቦቻቸውና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መፅናናትን ይመኛል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

HTML tags are not allowed.