ትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ የማህበረሰብ አገልግሎትን ለማሰፋፋት እንደሚጥሩ ምሁራን ተናገሩ

 

ሐረር መስከረም 14/2008 የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ የማህበረሰብ አገልግሎትን ለማስፋፋትና ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ምሁራንና የአስተዳደር ሰራተኞች ገለጹ። መምህራኑና የአስተዳደር ሰራተኞቹ  በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አፈጻጸምና በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ሲያካሄዱት የቆዩትን ውይይት ትናንት አጠናቀዋል።ተሳታፊዎች በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ እንዳሉት በቆይታቸው ያለፉትን ዓመታት የእቅዱን አፈጻጸም ስኬቶች ፣ የነበሩት ክፍተቶችን በመለየትና መሻሻል ያለባቸውን ጉዳዮች በመጠቆም ቀጣዩን መርሀ ግብር ከትምህርት ልማት አንጻር የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት የሚያግዛቸውን ግንዛቤ ጨብጠዋል።

በተለይ በተቋሙ የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥና የአካባቢውን ህብረተሰብ ሊጠቅሙ የሚችሉ የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎች ላይ ክፍተቶች እንደነበሩ በውይይታቸው ወቅት ማየታቸውን ተናግረዋል።በተቋሙ ለሚማሩ ተማሪዎች አፋጣኝ ምላሽ ያለመስጠት፣ስራን ማዕከል ያደረገና እቅድን ተመርኩዞ ስራዎች በወቅቱ ያለመከናወን በጉድለትነት መመልከታቸውን ተናግረዋል።እንዲሁም የውጭ ግንኙነት ስራዎች አናሳ መሆን፣ የልማት ሰራዊትን አደራጅቶና ስራን ማዕከል ያደረገ እንቅስቃሴ ላይ ድክመት መታየቱንም ጠቁመዋል።የነበሩባቸውን ክፍተቶች በማረም የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅና የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎችን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የተቀናጀ ጥረት እንደሚያደርጉም ምሁራኑ ገልጸዋል።በተቋሙ ውስጥ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራ የማጠናከር ፣በተማሪዎች መካከል ደግሞ የመቻቻልና የመከባበር ባህል እንዲጎለብትም ግንባር ቀደም ሆነው እንደሚሰሩም ተናግረዋል።መንግስት በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ሊተገብራቸው የያዛቸውን ዕቅዶች ለማሳካት በተሰለፉበት መስክ ጠንክረው በመስራት የድርሻቸውን እንደሚወጡ  ጠቁመዋል።

የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጨመዳ ፊኒንሳ ፣ የሐረሪ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንትና የዩኒቨርሲቲው የቦርድ አባል አቶ ረጋሳ ከፋለ በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ መንግስት ሊተገብራቸው ላቀዳቸው የልማት ስራዎች ስኬታማነት የመምህራን ድርሻ ከፍተኛ መሆን በየበኩላቸው በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል።አመራሩን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈጻጸም ወቅት የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን  በማጠናከርና ድክመቶችን በማረም ለተሻለ ውጤት መትጋት እንደሚጠበቅባቸውም አመልክተዋል።በዩኒቨርሲቲው ዋና ግቢ ፣ሐረርና ጭሮ ኮሌጆቹ ለአንድ ሳምንት በተካሄደው ውይይት ላይ የተቋሙ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች ተሳትፈዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

HTML tags are not allowed.