ተቋሙ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን በማስፈን የተጣለበትን ኃላፊነት በበለጠ እንዲወጣ የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች ገለጹ። መምህራኑና የአስተዳደር ሠራተኞቹ በመማር ማስተማር ሥራና በሀገሪቱ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ለስምንት ተከታታይ ቀናት ሲያካሂዱት የነበረው ስልጠናና ውይይት ትናንት ተጠናቋል።
በስልጠናው ማጠቃለያ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች በስልጠና ቆይታቸው በሀገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች፣ በትምህርት ተሳትፎና ጥራት ማሻሻል እንዲሁም በሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትና በልማት ሠራዊት ግንባታ ጠቀሜታ ላይ ግንዛቤያቸውን እንዳሳደጉ ተናግረዋል።

የዩኒቨርሲቲው የህግ መምህር የሆኑት አቶ ትግሉ መለሰ በተቋሙ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችና ብልሹ አሰራሮች፣ የትምህርት ጥራት መጓደል ምክንያቶችና ሌሎች ለመማር ማስተማሩ እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮች ተነስተው ውይይት መካሄዱንና የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።ተቋሙ የተሰጡትን የመማር ማስተማር፣ የማህበረሰብ አገልግሎትና የምርምር ሥራዎችን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ለሚያደርገው ጥረት የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽዎ ለማበርከት መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል።

“የተቋሙ ኃላፊነቶች እንዲሳኩ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ማስፈን ወሳኝ ነው” ያሉት መምህሩ፣ ለእዚህ እንደሚሰሩና በተማሪዎች መካከል የመቻቻልና የመከባበር ባህል እንዲጎለብት ጥረት እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።”የውይይት መድረክ በማዘጋጀት የመማር ማስተማር ሥራው ፍጹም ሰላማዊ እንዲሆን ያላሰለሰ ጥረት አደርጋለሁ” ብለዋል።
በዩኒቨርሲው የሶሺዎሎጂ መምህር አሸናፊ መብራቱ በበኩላቸው ፣ በስልጠናው በተማሪዎችና በመምህሩ መካከል የነበረውን መልካም ግንኙነቶችን ማጠናከር በሚቻልበት መንገድ ላይ ተወያይተው የጋራ ግንዛቤ ላይ እንደደረሱ አመልክተዋል።በውይይቱ ላይ በተነሱ ሀሳቦች በመታገዝ የመማር ማስተማሩን ሥራ ሰላማዊ የማድረግ እንዲሁም ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ሥራን በማጠናከር እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጨመዳ ፊኒንሳ በተቋሙ ለስምንት ቀናት የተካሄደው ስልጠና ሰላማዊና ሁሉም መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች ሀሳባቸውን በነጻነት የገለጹበት መድረክ መሆኑን አመልክተዋል።በውይይቱ ለተቋሙም ሆነ ለመንግስት ግብአት የሆኑ ሀሳቦች የተገኙበት መሆኑን ጠቅሰው፣ መምህሩና የአስተዳደር ሠራተኛው በዩኒቨርሲቲው የታዩትን ክፍተቶች ለመሙላት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል።በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ሚኒስትርና የዩኒቨርሲቲው የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ስለሺ ጌታሁን እንደተናገሩት፣ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማጠናከር የተቋሙ ማህበረሰብ በርካታ ስራዎችን ማከናወን አለበት።እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ በተለይ በተቋሙ አልፎ አልፎ የሚከሰቱ የሰላም ችግሮች ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መፍትሄ በሚያገኙበት ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥተው የመስራትና ችግሮች ሳይባባሱ በውይይት መፈታት አንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በተቋሙ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራ ማስፈን ሁሌም ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አመልክተው፣ መምህራን የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅና የምርምር ሥራዎችን በማጎልበት ብቁ ዜጋ ማፍራት እንዳለባቸው አስረድተዋል።በቀጣይም “አመራሩ፣ መምህራኑና የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በስልጠናውና በውይይቱ የተገኙ መልካም ተግባራትን በማጠናከርና በድክመት የተነሱትን በማሻሻል የጎላ ሥራ መስራት ይጠበቅባችዋል” ብለዋል።በዩኒቨርሲቲው ዋና ግቢና ሐረር ከተማ በሚገኘው ጤና ሳይንስና የሕክምና ኮሌጅ ለስምንት ቀናት በተካሄደው ስልጠናና የውይይት መድረክ ሁሉም የተቋሙ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች ተሳትፈዋል፡፡