በተቀናጀ የጎልማሶች ትምህርት አተገባበር ላይ ከተለያዩ አካባቢዎች ለመጡ ስልሳ ባለሞያዎች ስልጠና ተሰጠ፡፡

 

በግብርና ፣ በትምህርት ፣ በጤና ፣ በገቢ ማስገኛና በአካባቢ ጥበቃ ላይ ጎልማሶችን ለማስተማርና ለማብቃት ታቅዶ በአገር አቀፍ ደረጃ የጎልማሶች ትምህርት ፓኬጅ ተቀርጾ ወደ ስራ ተገብቷል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ስልሳ ለሚሆኑ ከድሬዳዋ መስተዳደር ፣ ከምስራቅ ሐረርጌና ከሐረሪ ክልል ለተውጣጡ የጎልማሶች ትምህርት አመቻች ባለሞያዎች ከታህሳስ 8 እስከ 10/2008 ዓ.ም ለሶስት ቀናት በጎልማሶች ትምህርት ፓኬጅ ይዘትና አተገባባር ላይ ስልጠና ሰጥቷል፡፡

1

በጎልማሶች ትምህርት እና ማህበረሰብ ልማት ትምህርት ክፍል መምህርና የስልጠናው አስተባባሪ የሆኑት አቶ ሲሳይ ማንያዘዋል ስልጠናውን አስመልክተው እንደተናገሩት የጎልማሶች ትምህርት የማህበረሰቡን ህይወት ማሻሻልን ማዕከል አድርጎ በ2003 ዓ/ም ተቀረጾ ወደ ስራ እንደተገባ አስታውሰው ስራውን ለመስራት የተሰማሩ ባለሞያዎች በቀጥታ በጎልማሶች ትምህርት አሰጣጥ ላይ ያልሰለጠኑና ከተለያዩ ሞያዎች የተውጣጡ በመሆናቸው በትግበራ ወቅት የግንዛቤና የክህሎት ውስንነት ሊያጋጥም እንደቻለ ገልጸዋል፡፡

3

አቶ ሲሳይ አያይዘው እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው ይህንን ክፍተት ለመሙላት እንዲያስችል አምና ተመሳሳይ ስልጠና ለከፍተኛ ኤክስፐርቶች እንደሰጠና ዘንድሮ ደግሞ ወደታች በመውረድ በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ ማዕከሎች ውስጥ በአመቻችነት ለሚሰሩ ባለሞያዎች የጎልማሶች ትምህርትን እንዴት በተቀናጀ መልኩ ማቀድ ፣ መተግበር ፣ መምራትና መመዘን እንደሚችሉ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ስልጠናን እየሰጠ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የስልጠናው ተካፋይ የሆኑት አቶ ፋንታሁን ቸርነትና ወ/ሮ ፍሬህይወት ታደሰ በበኩላቸው የተሰጣቸው ስልጠና በስራ ላይ ያጋጠማቸውን ችግር መሰረት ያደረገ በመሆኑ ለቀጣይ ስራ አቅም እንደፈጠረላቸው ገልጸው ከዚህ ቀደም  ጎልማሶችን በምን መልኩ መቅረብ ፣ እንዴትና መች ማስተማር እንደሚገባ  ካለመረዳት ጋር ተያይዞ ክፍተቶች እንደነበሩባቸው ተናግረዋል፡፡ አሁን ከተሰጠው ስልጠና በተጨማሪ እርስበርስ የልምድ ልውጥ በማድረግ ግንዛቤያቸውን ለማዳበር እንደቻሉ ተናግረዋል ፡፡

2

በስልጠናው የመዝጊያ ስነ-ስርአት ላይ በጎልማሶች የትምህርት ፓኬጅ የተቀመጠው ግብ በተሟላ መልኩ ተግባራዊ መሆን እንዲችል ሰልጣኞች በስልጠና ወቅት ያገኙትን እውቀትና ልምድ ለሌሎች ማካፈልና በየአካባቢያቸው ከሚገኙ ባለሞያዎች ጋር ተቀናጅቶ መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተገልጿል፡፡

4

በጎልማሶች ትምርት ላይ በማተኮር ለሶስት ቀናት በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ሐረር ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የተሰጠውን ስልጠና የዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ ልማት ዳይሬክቶሬት ከትምህርትና ስነ-ባህሪ ኮሌጅ ጋር በመተባበር አዘጋጅተውታል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

HTML tags are not allowed.