በምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ የሚገኙ ነዋሪዎች የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ህግ ኮሌጅ በአካባቢያቸው እየሰጠ በሚገኘው ነጻ የህግ ድጋፍ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገለጹ፡፡

 

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ህግ ኮሌጅ በምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ እንዲሁም በሐረሪ ክልል በሚገኙ ፍርድቤቶችና ማረሚያ ቤቶች ውስጥ አርባ ሁለት የህግ ድጋፍ መስጫ ቢሮውችን በመክፈትና የህግ ባለሞያዎችን በመቅጠር የገንዘብ አቅም ለሌላቸውና ለጥቃት ተጋላጭ ለሆኑ ወገኖች ነጻ የህግ ድጋፍ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል ፡፡

a

በህግ ድጋፍ አገልግሎቱ ተጠቃሚ ከሆኑ ሰዎች መካካል በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ቦኬ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት ሼክ መሐመድ አህመድ የወደቀ የኤሌትሪክ ፖል ባደረሰባቸው አደጋ እጃቸው ላይ ጉዳት መድረሱንና በዚሁ ምክንያትም የቀኝ እጃቸውን ሊያጡ እንደቻሉ ይናገራሉ፡፡ ለደረሰባቸው ጉዳትም ክስ መስርተው የሚመለከተውን አካል ካሳ ለመጠየቅ ቢነሱም ድርጅቱ ጠበቃ አቁሞ የሚከራከር በመሆኑና እሳቸውም በራሳቸው ፍርድ ቤት ቆሞ ለመከራከር የህግ ዕውቀት የሌላቸውና ጠበቃ ገዝተው ለማቆምም አቅም ያልነበራቸው በመሆኑ ተስፋ ቆርጠው ባሉበት ወቅት ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ አካል ጉዳተኞ ለሆኑ ሰዎች ነጻ የህግ ድጋፍ እንደሚሰጥ ሰምተው አካባቢያቸው ወደሚገኘው ማዕከል መሄዳቸውን ይገልጻሉ ፡፡

a1

ዩኒቨርሲቲው ያስቀመጠውን ጠበቃ አግኝቼ የደረሰብኝን ከነገርኩት በኃላ ያለምንም ክፍያ ፍርድ ቤት ቆሞ እንደሚከራከርልኝ ሲነግረኝ ደስታዬ ወደር አልነበረውም ፡፡ በአሁኑ ወቅት እንኳን ጥብቅና ቆሞ መከራከር አይደለም የህግ ምክር እንኳን የሚገኘው በክፍያ በመሆኑ እንደዚህ አይነት እድል አገኛለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር ፡፡ መረጃዎችን በማሰባሰብ ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በኔ ቦታ ሆኖ እስከ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ድረስ በራሱ ወጪ ተከራክሮልኝ መብቴን አስከብሮልኛል፡፡ ፍርድቤትም ለደረሰብኝ ጉዳት 180‚000 ብር ከሳ እንዲከፈልኝ ፈርዶልኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት ይህንን ብር ተቀብዬ አንድ ባጃጅ መኪና ገዝቼ እየሰራች የምትገኝ ሲሆን በቀረው ብርም ከብቶች ገዝቼ በማደለብና በመሸጥ እየተዳደርኩ እገኛለሁ፡፡ ተስፋ ከቆረጥኩበት ተነስቼ እዚህ እንድደርስ ከጎኔ ቆሞ ለደገፈኝ ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡

a2

የህግ ኮሌጁ እየሰጠ በሚገኘው የህግ ምክር ፣ ክስና መልስ የመጻፍ እንዲሁም በፍርድ ቤት ቆሞ የመከራከር ነጻ ህግ ድጋፍ አገልግሎት ከፍተኛውን ድርሻ በመውሰድ ተጠቃሚ እየሆኑ የሚገኙት ሴቶች መሆናቸውን ከአገልግሎት መስጫ ቢሮዎቹ የሚሰበሰቡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በነዚህ ቢሮች አገልግሎት ካገኙ ሴቶች መካከል በቀርሳ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ በድሪያ አሜ አንዷ ሲሆኑ ከዚህ ቀደም ከባለቤታቸው ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ባለቤታቸው ከነልጆቻቸው ከቤት እንዳስወጣቸውና አልፎ ተርፎም የሚገባቸውን ንብረት ሳይካፈሉ ባፈሩት ንብረት ላይ ሌላ ሚስት አግብቶ መኖር እንደጀመረና እሳቸውም የቀን ስራ እየሰሩ ለሁለት ዓመት ያህል የድርሻቸውን ንብረት ለማግኘት ሲጥሩ ቆይተው ስላልተሳካላቸው ሀገር ለቀው ለመሄድ በተነሱበት ወቅት ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ መብታቸውን ላጡ ሴቶች መብታቸው እንዲከበር ድጋፍ የሚሰጥበት ቢሮ በወረዳው እንዳለ ሰምተው ወደ ቢሮው መሄዳቸውን ይናገራሉ፡፡

“ ዩኒቨርሲቲው ወደ ከፈተው ቢሮ ሄጄ አገልግሎት ለምትሰጠው ልጅ ሁለት አመት ሙሉ ከነልጆቼ የደረሰብኝ ከነገርኳት በኃላ በጣም አዝና ከጎኔ ቆማ እንደምትከራከርልኝ ስትነግረኝና ስታበረታታኝ ሀቄን ያገኘው ያህል ነበር የተሰማኝ፡፡ ከብዙ ክርክርና ሂደት በኃላ የሚገባኝን ንብረት እንድካፈል ተፈርዶልኝ ይህው አሁን የምኖርበት ቤትና የእርሻ መሬት አግኝቼ ያንን እያረስኩ ከልጆቼ ጋር በደስታ እየኖርኩ እገኛለሁ፡፡ ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በኔ ቦታ ሆኖ ባይከራከርና መብቴን ባያስከብርልኝ ኖሮ ከነ ልጆቼ ሜዳ ላይ ወድቄ በቀረሁ ነበር፡፡ ዩኒቨርሲቲው ላደረገልኝ ሁሉ እያመሰገንኩ ይህ አገልግሎት ብዙ ሰዎች መብታቸው እንዲከበር እየደገፈ የሚገኝ በመሆኑ በዚሁ እንዲቀጥል እጸልያለሁ፡፡ ”

a3

ይህ የህግ ድጋፍ አገልግሎት መሰጠት ከተጀመረበት ከ2006 ዓ/ም ጀምሮ እስከ ጥቅምት ወር 2009 ዓ/ም ድረስ 126‚180 የህግ ድጋፍ የሚሹ ሴቶችና ህጻናት ፣ አረጋውያን ፣ አካል ጉዳተኞች ፣ ኤች አይ ቪ በደማቸው የሚገኝ ወገኖች እና ታራሚዎች የዚህ አገልግሎት ተጠቃሚ በመሆን መብታቸውን በህግ ፊት ለማስከበር ችለዋል፡፡

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ህግ ኮሌጅ የፍትህ ተደራሽነትና ህግ ንቃት ፕሮጀክት (AJLA) በተለያዩ አካባቢዎች ቢሮዎችን ከፍቶ ከሚሰጠው የህግ ድጋፍ አገልግሎት በተጨማሪ የህግ ግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርትና ስልጠናዎችን በመስጠት እንዲሁም የህግ ጥናቶችን በማካሄድ እየሰራ ይገኛል ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

HTML tags are not allowed.