በማህበር ለተደራጁ ወጣቶች የዳቦ መጋገሪያ ማሽን ድጋፍ ተደረገ

 

የሐረማያ ዩኒቨረሲቲ ግምቱ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የዳቦ መጋገሪያ ማሽን በማህበር ለተደራጁ ወጣቶችና ለባቴ ከተማ ማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ ድጋፍ አደረገ፡፡ ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅት ከመማር ማስተማር፤እንዲሁም ጥናትና ምርምር ከማካሄድ ጎን ለጎን ማህበረሰብ አቀፍ ለውጦችን ሊያመጡ የሚችሉ የድጋፍ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡

 

በተለይም  ዩኒቨረሲቲው ለህብረተሰቡ በትምህርት፤ በግብርና፤ በወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራና መሰል ተግባራት ዙሪያ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡የዚሁ የማህበረሰብ ድጋፍ አንድ አካል የሆነውና የአካባቢውን ወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራን ለመደገፍ የሚያስችል የዳቦ መጋገሪያ ማሽን ለኢፋ-ቦሩ ማህበር አባላት ድጋፍ አድርጓል፡፡ የካቲት 15 ቀን 2010 ዓ.ም በተደረገው የድጋፍ አሰጣጥ ስነ-ስርዓት ላይ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጨመዳ ፊኒንሳ እንደተናገሩት የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ለአካባቢው ማህበረሰብ ግልጋሎት የሚሰጡ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልፀው በማህበር የተደራጁ ወጣቶችን ለመደገፍ ዩኒቨርሲቲው ይጠቀምበት የነበረውን የዳቦ መጋገሪያ ማሽን ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

  

የተደረገው የዳቦ መጋገሪያ ማሽን ድጋፉ በአሁኑ ገበያ የገንዘብ ተመን ከ1000000.00 (አንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡  የዳቦ ምርት ገበያ ያለውና በአካባቢው ያለውን ፍላጎት ማሟላት ያልተቻለ በመሆኑ እናንተም ይህንን የወሰዳችሁትን ማሽን በስነ-ስርዓት ተጠቅማችሁ የአቅርቦት ፍላጎቱን ለማሟላት
እንድትጥሩ ሲሉ ፕሮፌሰር ጨመዳ ለማህበሩ አባላት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

  

ድጋፍ የተደረገለት የኢፋ-ቦሩ የዳቦ አምራች ማህበር ሊቀመንበር ወጣት ሐምዛ ጀማል እንደተናገረው የማህበራቸው አባላት ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች በተመረቁ አስር አባላት ተደራጅተው በዳቦ ምርት ላይ ለመሰማራት መዘጋጀታቸውን ገልጾ የተደረገላቸው የዳቦ መጋገሪያ ማሽንም “ የወጣቶችን ስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዘና የማህበሩ አባላትንም ስራ የሚያስጀምር በመሆኑም ” ዩኒቨርሲቲው ላደረገላቸው ድጋፍ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ለባቴ አካባቢ ቀበሌ መስተዳድር የአካባቢውን ሠላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ እየሰራ ላለው የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ ሥራን የሚያግዝ አንድ የሞተር ሳይክል ድጋፍ አድርጓል፡፡የሞተር ሳይክሉን ቁልፍም የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጨመዳ ፊኒንሳ ለባቴ አካባቢ ቀበሌ ሊቀመንበር አስረክበዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ያደረገውን ድጋፍ አስመልክተው የባቴ አካባቢ ቀበሌ አፈ-ጉባኤ አቶ ዘነበ ጅራኔ እንደተናገሩት ዩኒቨረሲቲው ለአካባቢው ማህበረሰብ ያደረገው የዳቦ መጋገሪያ ማሽን እና የሞተር ሳይክል ድጋፍ ዩኒቨርሲቲያችን አቅሙ በፈቀደ መጠን እየረዳን መሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል፡፡  ዩኒቨርሲቲው በቀጣይም በተለያዩ ዘርፎች የሚያደርግልንን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተስፋ አለኝ ብለዋል፡፡

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አገልግሎትና የኢንተርፕራይዝ ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ከበደ ወልደፃዲቅ በበኩላቸው ሞያዊ ድጋፍን ጨምሮ ተመሳሳይ የህብረተሰቡን ህይወት ሊቀይር የሚችል ድጋፎችን አቅም በፈቀደ መልኩ ዩኒቨርሲቲው እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

HTML tags are not allowed.