የመልካም አስተዳደር መጎደል በስፋት ከሚስተዋልባቸው የአገልግሎት ዘርፎች መካከል የመሬት አስተዳደር አንዱ ነው፡፡ እንደ ሀገርም ይህንን ችግር ለመቅረፍ የአገልግሎት ሰጪ ባለሞያዎችን በማሰልጠንና በማስተማር የተጣለባቸውን ሀላፊነት በሚገባ ተገንዝበው ሞያዊ ስነምግባር የተላበሰ አገልግሎት እንዲሰጡ መስራትና ማብቃት እንደ ዋነኛ አማራጭ የተወስደ መንገድ ነው፡፡

ይህንን መሰረት በማድረግም የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ስራዎች ዳይሬክቶሬት ከምስራቅ ሐረርጌ የተለያዩ ወረዳዎች ለተውጣጡ ሰላሳ(30) የመሬት አስተዳደር ሰራተኞች ለሁለት ቀናት በሁለት እርዕሶች ላይ ማለትም በመልካም አስተዳደርና በሙስና መከላከል ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቶል፡፡

ስልጠናው በዋነኛነት ከመሬት አስተዳደር ጋር ተይዞ የመልካም አስተዳደር መስፈንና መጓደል መገለጫዎች ምንድናቸው ፣መልካም አስተዳደር እንዴት ሊዳብር ይችላል ፣ ሙስና በግለሰብም ሆነ በሀገር ላይ የሚያሰከትለው ጉዳት ምንድነው ፣ ሙስናን እንዴት መከላከልና መዋጋት ይቻላል በሚሉ ጉዳዮች ላይ በማተኮር በዩኒቨርሲቲው መምህራን የተሰጠ ነው፡፡

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር አድማሱ ቦጋለ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝና በተለይም በማህበረሰብ ልማት ዳይሬክቶሬት ስር ያለውን የተማረ የሰው ሐይል በማስተባበር በግብርና ፣ በትምህርት ፣ በጤናና በሌሎችም የአግልግሎት ዘርፎች ላይ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ሊደርጉ የሚችሉ በርካታ የአቅም ግናባታ ስልጠናዎችን እየሰጠ ይገኛል ፡፡

በዕለቱ የተሰጠው ስልጠናም በመሬት አስተዳደር ላይ የሚሰሩ ባለሞያዎች ከመሬት ጋር ተያይዞ አገልግሎት በሚሰጡበት ወቅት እራሳቸውን ከሙስና በመጠበቅ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለተገልጋዮች ለመስጠት እንዲችሉ አቅም የሚፈጥርና እርስ በእስርም ልምድ ለመለዋወጥ እንዲችሉ እድል የሚሰጥ መድረክ እንደሆነም ዶ/ር አድማሱ ገልጸዋል፡፡

የስልጠናው ተካፋይ የሆኑት አቶ መሐመድ ዩሱፍ በበኩላቸው በማህበረሰቡ ዘንድ የመሬት ጉዳይ እጅግ አንገብጋቢ በመሆኑ በጥንቃቄና ፍትሀዊ በሆነ መልኩ አገልግሎት መስጠት አስፈላጊ እንደሆነ ጠቅሰው እንደዚህ ያሉ ስልጠናዎችም ባለሞያው ለሙስና ሊያጋልጡ ከሚችሉ አካሄዶችና አሰራሮች ተቆጥቦ የተጣለበትን ሀላፊነት እንዲወጣ ለማንቃትና ለማበረታታት እንዲሁም ተሞክሮዎችን ለመለዋወጥ ትልቅ አስተዋጾ የሚያደርጉ በመሆናቸው ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡