በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተቋርጦ የነበረው የመማር ማስተማር ስራ ሙሉ በሙሉ መጀመሩን ዩኒቨርሲቲው አስታወቀ።

የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ንጉሴ ደቻሳ ለኢዜአ እንደገለጹት በዩኒቨርሲቲው የሚገኙ ተማሪዎች ባቀረቡት የተለያየ ጥያቄ በተቋሙ ለተወሰነ ጊዜ ትምህርት ተቋርጦ ነበር።

ተማሪዎች ላነሱት ጥያቄዎች ተቋሙን የሚመለከቱት ተገቢ ምላሽ እንደሚሰጥና ሌሎች ጥያቄዎችን ደግሞ ለሚመለከተው አካል የማሳወቅ ስራ በማከናወን ከህዳር 9/2010 ጀምሮ የመማር ማስተማር ስራ ተጀምሮ ሰላማዊ በሆነ መንገድ እየተከናወነ ነው።

”በአሁኑ ወቅትም 90 በመቶ የሚሆኑ የተቋሙ ተማሪዎች መማሪያ ክፍል ገብተው ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ነው” ብለዋል።

የባከኑ የትምህርት ጊዜያትን ለማካካስም ቅዳሜ ቀንን የስራ ሰዓት ለማድረግ፣ በሴሚስተር መካከል የተማሪዎችን የእረፍት ጊዜ ለማሳጠርና አዲስ የትምህርት ፕሮግራም ለማውጣት ከመምህራንና ተማሪዎች ጋር ስምምነት መድረሱን ተናግረዋል።

የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ህብረት የህዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ ተማሪ ሄኖክ ተሬቻ በበኩሉ ተማሪዎች ወደ ግቢ እንዲገቡና የተቋረጠው ትምህርት እንዲጀመር ህብረቱ ከሚመለከተው አካል ጋር ያከናወነው ተግባር ውጤት አስገኝቷል፡፡

በአሁኑ ወቅትም የመማር ማስተማር ስራው ሰላማዊ በሆነ መንገድ በመካሄድ ላይ መሆኑን ተናግሯል፡፡

”ትምህርት በመቋረጡ ከፍተኛ የጊዜ ኪሳራ ገጥሞናል፤ በዚህም በአሁኑ ወቅት እየተጨናነቅንና በተጣበበ ጊዜ ትምህርት እንድንከታተል አድርጎናል” ያለው ደግሞ የጋዜጠኝነትና ህዝብ ግንኙነት የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ሳሙኤል ጆንሲ ነው።

”ማንኛውም ጥያቄ ትምህርት ሳይቋረጥ በሰላማዊና በሰለጠነ  መንገድ መፍታት እንደሚገባ ግንዛቤ አግኝቻለሁ” ብሏል፡፡

”የትምህርቱ መቋረጥ መደነጋገር ፈጥሮብኛል” ያለው የአንደኛ ዓመት የኮንፒተር ሳይንስ ተማሪ ምስክር በለጠ በበኩሉ ”ትምህርት በመጀመሩ ተደስቻለሁ ለሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት መጠናከር እንዲሰፍን የበኩሌን እወጣለው” ብሏል።

በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን ከ13ሺ በላይ ተማሪዎች በመደበኛው የትምህርት ፕሮግራም ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ነው።