በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ለተማሪዎች የተዘጋጀ ስልጠና ተጀመረ

 

(ምንጭ፡- ኢዜአ)ሀረር ነሐሴ 16/2006

በሐገሪቱ በየዘርፉ እየተከናወነ ያለውን የሕዳሴ ጉዞ ለማጎልበት የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪዎችን አቅም መገንባት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑ ተገለጸ።

ለሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በሀገራዊና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የተዘጋጀ ስልጠና ትናንት ተጀምሯል።

IMG_4319

በስልጠናው መክፈቻ ወቅት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የካቢኔዎች ጉዳይ ሚኒስትር አቶ እሸቱ ደሴ እንደተናገሩት መንግሰት የልማት፣የመልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታን ለማጎልበት የቀረጸው ፓሊስና ስትራቴጂ በሀገሪቱ አበረታች የኢኮኖሚ እድገት እንዲመዘገብ አስችሏል።

በሀገሪቱ እስካሁን ለተገኘው እድገት ከከፍተኛ አመራር እስከ ማህበረሰቡ የተካሄደው የማስፈጸም የዓቅም ግንባታ ስልጠና ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።

መንግስት ዴሞክራሲን ከመገንባት፣የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማጠናከር የመቻቻልና መከባበር ባህል ከማዳበር አኳያ ያከናወነውና ያጋጠሙ ችግሮችን ለማስወገድ ያከናወናቸውን ስራዎች ለከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪዎች ማሳወቅ ተገቢ መሆኑ አስታውቀዋል።

IMG_4350

ስልጠናው የነገው ሀገር ተረካቢ ወጣት በትምህርት ተቋም ቆይታው የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን የሚያደፈርሱና በመማር ማስተማሩ ስራ ላይ ሊከሰት የሚችለውን ችግር በራስ ተነሳሽነትና በዴሞክራሲያዊ  መንገድ ለማስወገድ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

ተማሪዎች የከፍተኛ ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ስራ ዓለም ሲገቡ መልካም ስነ ምግባር የተላበሱ፣ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት እንዲችሉ፣ ህብረተሰቡን በቅንነትና በታማኝነት በማገልገል ውጤታማ እንዲሆኑ ስልጠናው እንደሚያግዛቸው አስታውቀዋል።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዜዳንት ዶክተር ግርማ አመንቴ በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው ለአስራ አምስት ቀናት በሚሰጠው የዓቅም ግንባታ ስልጠና ላይ ከምስራቅ ሸዋ፣ከምዕራብና ምስራቅ ሐረርጌ ዞንና ከሐረሪ ክልል የተውጣጡ ስድስት ሺህ 700 የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው ብለዋል።

በመጪው የትምህርት ዘመን በሚጠብቃቸው ኃላፊነት፣በመንግስት ፖሊሲና ስትራቴጂ ላይ በዩኒቨርሲቲው ዋናውን ግቢ ጨምሮ በሐረርና ጭሮ ከተማ ኮሌጆች ሰባት አዳራሾች ለስልጠናው መዘጋጀታቸውን  አስታውቀዋል።

የተማሪዎቹ እንደተጠናቀቀም በተቋሙ ለሚገኙ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች ስልጠናው እንደሚቀጥል ዶክተር ግርማ ተናግረዋል።

በዩኒቨርስቲው የ3ኛ ዓመት የሲቪል ኢንጅነሪንግ ተማሪ ትግስት ምትኩና የመንዝወርቅ በላይሁን ስልጠናው መዘጋጀቱ መንግስት እያከናወነ ያለውን የልማት ስራ ተማሪው ተገንዝቦ የነገ ኃላፊነቱን በአግባቡ ለመወጣት ዝግጁ እንደሚሆን ተናግረዋል።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በ2006 የትምህርት ዘመን በመደበኛ፣በተከታታይ፣በርቀትና ክረምት የትምህርት መርሃ ግብር ከ34 ሺህ የሚበልጡ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ መሆኑ መገለጹ ይታወሳል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

HTML tags are not allowed.