በሐረማያ ሐይቅ ተፋሰስ ልማት ዙሪያ ውይይት ተደረገ

 

በኢብሒም ሰዒድ(ህዝብና አለማቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት)

በተለያዩ ምክንያቶች  የጠፋውን የሐረማያ ሐይቅ ወደ ቀድሞው ይዞታ ለመመለስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ የሚገኘው ግብረሀይል በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ባካሄደው የግማሽ ቀን ውይይት እስካሁን ያከናወናቸውን ተግባራትና ወደፊት መሰራት ባለባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል፡፡

በውይይቱ ላይ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጨመዳ ፊኒንሳን ጨምሮ ምክትል ፕሬዚዳንቶች የኮሌጅ ዲኖች፣ጉዳዩ የሚመለከታቸው ትምህርት ክፍል ኃላፊዎች እንዲሁም ከሐረማያ ከተማ፣ ከሐረማያ ወረዳና ከምስራቅ ሐረርጌ ዞን የተውጣጡ የስራ ኃላፊዎችና አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል፡፡

1

ፕሮግራሙ የተጀመረው ገንደሙዴ አካባቢ ያለውንና የደረቀውን የሐይቁን ክፍል በመጎብኘት ሲሆን በእለቱ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የማሀበረሰብ አቀፍና ኢንተርፕራይዝ ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ከበደ ወ/ጻዲቅ ምንም እንኳን የተፋሰስ ልማት ፕሮጀክቱ ከተጀመረ 3ኛ አመቱን ቢይዝም ከወረዳው እና ከዞኑ የሚመለከታቸው አካላት የሚደረገው ድጋፍ አናሳ በመሆኑ ባሰበነው ፍጥነት ለመራመድ አልቻልንም ብለዋል፡፡

ይህ ፕሮጀክት ያለህዝቡና የመንግስት አካላት ቁርጠኛ ተሳትፎ ግቡን እንደማይመታ ከወዲሁ በማመን በጋራ ካልተሰራ አይደለም ሐይቁን ማሰመለስ ለመጠጥ የምናውለው የከርሰ-ምድር ውሀ ባጭር ጊዜ ውስጥ ሊደርቅ እንደሚችል አሳስበዋል፡፡

በገንደሙዴ የተደረገው የመስክ ጉብኝት እንደተጠናቀቀ በዩኒቨርሲቲው የስልጠና ማዕከል የሐረማያ ሐይቅ የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ጽ/ቤት የ2007 የስራ አፈጻጸም ሪፖርት በአቶ ተፈሪ ታደሰ ቀርቧል፡፡ ጽ/ቤቱ ሐይቁን ከማሰመለስ ባሻገር በሰባት ዋና ዋና ዘርፎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ ህዝቡንና ገበሬውን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራትን ማከናወኑን ከተደረገው ገለጻ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ ከነዚህም መካካል በአፈርና ውሃ እቀባ፣ በንብ ማነብ፣ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ፣ ስነ-ተዋልዶ ጤናን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ በነዚህም ዘርፎች ላይ ትርጉም ያለው ስራ ቢሰራም በተከሰተው የቅንጅት እና የትኩረት ማነስ ምክንያት ያስገኙት ውጤት ሲመዘን አንደተጠበቀው አይደለም ተብሏል፡፡

የፕሮጀክቱ ኃላፊ ዶ/ር አብዱለጢፍ አህመድ በበኩላቸው በፎቶግራፍ የተደገፈ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን ሐይቁ ይመለስበታል ተብሎ እየተሰራበት ያለው የተንጣለለ ሜዳ ገበሬዎቹ ለሰብል ምርት እየጠቀሙበትና እያረሱት በመሆኑ ስራቸው ላይ እንቅፋት እንደፈጠረባቸው አስረድተዋል፡፡2

ሁለቱ ምሁራኖች ባቀረቡት ገለጻ እንዲሁም በተቀናጀ የተፋሰስ ልማቱ እጣፋንታ ዙሪያ በዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት በፕሮፌሰር ጨመዳ ፊኒንሳና ከሐረማያ ወረዳና ከምስራቅ ሐረርጌ ዞን በሙጡ እንግዶች መሪነት ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጓል፡፡ ፕ/ር ጨመዳ በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት ይህ ፕሮጀክት በዋነኝነት ባለቤትነቱ የህዝቡ መሆኑን በመግለጽ በየደረጃው ያሉ የስቲሪንግ ኮሚቴ እና የመንግስት መዋቅሮች ለተፈጻሚነቱ በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ ይገባል ብለዋል፡፡

ከሐረማያ ወረዳና ከምስራቅ ሐረርጌ ዞን የመጡ ተወካዮችም የቅንጅትና መዋቅር ችግር መኖሩን ያመኑ ሲሆን ወደፊት ተናቦና ተቀራርቦ ለመስራት ቃል ገብተዋል፡፡ በእለቱ ተወያዮችም ለተፋሰስ ልማቱ ውጤታማነት ይጠቅማሉ ያሏቸውን ሃሳቦች አቅርበዋል፡፡ በመጨረሻም አጋጠሙ የተባሉት ችግሮች ላይ ለመምከርና መፍትሔ ለመስጠት  የተፋሰሱ ስቲሪንግ ኮሚቴ ባጭር ጊዜ ውስጥ ስብሰባ እንዲያደርግ የውሳኔ ሀሳብ ተላልፈዋል፡፡ ለግማሽ ቀን የተካሄደው ውይይት የተቋጨው ለሐረማያ ሐይቅ የተፋሰስ ልማት ፕሮጀክት በመቅረጽና በልዩልዩ ዘርፎች አስተዋጽኦ ላደረጉ ግለሰቦች የምስጋና ምስክር ወረቀት በመስጠት ነበር፡፡

3

Leave a Reply

Your email address will not be published.

HTML tags are not allowed.