ሰላማዊ የትምህርት ስራን በማጠናከር የሀገሪቱ ልማት ለማፋጠን እንደሚጥሩ ምሁራን ገለጹ

 

ሐረር  ጥቅምት 1/2007 /የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት/  ሰላማዊ  የመማር  ማስተማርን  ስራ  በማጠናከር   የሀገሪቱን  ልማትና  የህዳሴ  ጉዞን  ለማፋጠን  የበኩላቸውን  ጥረት  እንደሚያደርጉ  በሐረማያ  ዩኒቨርሲቲ  በስልጠና  ላይ  የቆዩ  አንዳንድ  ምሁራን  ገለጹ፡፡

በመንግስት  ፖሊሲዎችና  ስትራቴጂዎች  ላይ  ለዩኒቨርስቲው  ምሁራንና  የአስተዳደር  ሰራተኞች  ለ 10  ቀናት  ሲሰጥ  የቆየው  ስልጠና  ሰሞኑን  ተጠናቋል፡፡

በዩኒቨርስቲው  የጆግራፊና  አካባቢ  ጥናት  ትምህርት  ክፍል  ሃላፊ  መምህር  አንተነህ  ደርበው  እንደተናገሩት  የትምህርትና  ሌሎችንም  የሀገሪቱ  የልማት  ፕሮግራሞች  የሚመሩበት  ፖሊሲዎችና  ስትራቴጂዎች  ላይ  ግንዛቤያቸውን  እንዲያሳድጉ  ስልጠናው  ረድቷቸዋል፡

እንዲሁም  ሰላማዊ  የመማር  ማስተማርና  ችግር  ፈቺ  የምርምር  ስራዎችን  አጠናክረው  ብቃት  ያለው  የሰለጠነ  የሰው  ሃይል  በማፍራት  ለሀገሪቱ  ልማትና  እድገት  የበኩላቸውን  ለመወጣት  የተሻለ  መነቃቃትና  ትልቅ  አቅም  እንደፈጠረላቸውም  ገልጸዋል፡፡

0

የተፈጥሮና  ኮምፒዩቲሽን  ሳይንስ  ኮሌጅ  መምህር  ሙሉጌታ  ደስታ  በበኩላቸው  በስልጠናው  ሂደት  ከቀረቡላቸው  አጀንዳዎች  በመነሳት  ሀሳባቸውን  በነጻነት  በማንሸራሸርና  ያልተገባቡበትን  ጉዳዮች  በልዩነታቸው  ይዘው  መከራከራቸውንና  ሂደቱም  ዴሞክራሲያዊ  እንደነበረ  ተናግረዋል፡፡

በተለይ   የመልካም  አስተዳደር ፣  የኪራይ  ሰብሳቢነትና  ሌሎች  ችግሮችን  ግልጽነትና  ተጠያቂነት  ያለው  አሰራር  በማስፈን  መፈታት  እንደሚቻል  በስልጠናው  ወቅት  በነበረው  ክርክርና  የጋራ  ውይይት  መገንዘባቸውን  አመልክተዋል፡፡

እንዲሁም  በመምህራን  ልማት ፣ በትምህርት  እድል  አሰጣጥ ፣ በትምህርት  ጥራትና  በሌሎች  ትምህርት  ነክ  በሆኑ  ጉዳዮች  ላይ  ልዩ  ትኩረት  ሰጥተው  መወያየታቸውንና  በልዩነቶችም  ላይ  የጋራ  መግባባት  ላይ  መድረሳቸውን  ተናግረዋል፡፡

ለሀገሪቱ  የልማት  ጉዞ  እንቅፋት  የሆኑትን  ጠባብነት ፣ ትምህክተኝነት ፣ የሀይማኖት  አክራሪነትን  በመታገል  የተጀመረውን  ልማት  ተጠናክሮ  እንዲቀጥል  የበኩላቸው  ድጋፍ  እንደሚያደርጉ  ገልጸዋል፡፡

ብሔር  ብሔረሰቦችና  ህዝቦች  ህገ  መንግስቱ  ያጎናጸፋቸውን  ዴሞክራሲያዊና  ሰብአዊ  መብቶች  ተጠብቆ  እንዲኖር  የድርሻቸውን  እንደሚወጡ  ምሁራኑ  አመልክተዋል፡፡

ህገ  መንግስቱን  በሃይል  ለመጣስ  የሚሞክሩና  ተማሪዎችን  የጸብ  መነሻ  በማድረግ  ድብቅ  የፖለቲካ  አጀንዳቸውን  ለማራመድ  የሚሞክሩ  የጸረ  ሰላምና  ጸረ  ልማት  ሃይሎችን  ተግባር  ነቅተው  እንደሚጠብቁ  ተናግረዋል።

በተለይም  በተቋማቸው  ሰላማዊ  የመማር  ማስተማርን  ስራ  በማጠናከር   የሀገሪቱን  ልማትና  የህዳሴ  ጉዞን  ለማፋጠን  የበኩላቸውን  ጥረት  እንደሚያደርጉም  ምሁራኑ  በሰጡት  አስተያየት  ገልጸዋል፡፡
00

በጠቅላይ  ሚኒስትር  ጽህፈት  ቤት  የካቢኔዎች  ጉዳይ  ሚኒስትር  አቶ  እሸቱ  ደሴ  ስልጠናው  መምህራን  በከፍተኛ  ትምህርት  ተቋም  የሚማሩ  ተማሪዎች  የመቻቻልና  የመከባበር  ባህልን  በማዳበርና  መንግስት  የጀመረውን  የልማት  ስራ  አጠናክሮ  እንዲቀጥል  እድል  የከፈተ  መሆኑን  አስረድተዋል፡፡

የሐረማያ  ዩኒቨርሲቲ  ፕሬዝዳንት  ዶክተር  ግርማ  አመንቴ  በበኩላቸው  ስልጠናው  መምህራን   የሀገሪቱ  ህዝቦች  ያሳለፏቸውን  የትግል  እንቅስቃሴና  ወቅታዊ   የልማት  አቅጣጫዎችን  ተገንዝበው  በህዳሴ  ጉዞ  ላይ  ንቁ   ተሳታፊ  እንዲሆኑ  መነቃቃትና  ትልቅ  አቅም  የፈጠረላቸው  መሆኑን  ተናግረዋል።

በስልጠናው  ላይ  800  ያሀል  ምሁራንና  የአስተዳደር  ሰራተኞች  የተሳተፉ  ሲሆን  በቆይታቸውም  በሀገሪቱ  ፖሊሲዎችናስትራቴጂዎች  እንዲሁም  በወቅታዊ  ጉዳዮች  ዙሪያ  ሰፋ  ያለ  ውይይት  በማደረግ  የጋራ  ግንዛቤና  መግባባት  ላይ  መድረሳቸውን  አመልክተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

HTML tags are not allowed.