መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና ሙስናን ለመከላከል እንደሚሰሩ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎች ገለጹ

 

መ

ሐረር ኢዜአ ግንቦት 17/2009 መንግስት መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና ሙስናን ለመከላከል የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ለማስቀጠል  እንደሚሰሩ  የሐረማያ  ዩኒቨርሲቲ  የዘንድሮ  ዓመት  እጩ  ተመራቂ  ተማሪዎች ገለጹ። ዩኒቨርሲቲው ለዘንድሮ ዕጩ ተመራቂ  ተማሪዎቹ  ሙስናን  መከላከል  በሚቻልበት  መንገድ፣ በመልካም  አስተዳደርና  በስነ ምግባር  ጽንሰ  ሃሳቦች ላይ  የሰጠው ስልጠና  ተጠናቋል። በስልጠናው  ከተሳተፉት  ተማሪዎች  መካከል የአምስተኛ ዓመት የህግ ተማሪ አማኑኤል ተሬሳ እንደገለጸው ተማሪዎች  መልካም  ስነ ምግባርን  ከመላበስ  ጀምሮ  መንግስት በተለያዩ  ተቋማት የሚታዩትን  የመልካም አስተዳደርና የሙስና ችግሮችን ለመከላከል እያከናወነ የሚገኘውን ጥረት ማጠናከር እንዳለባቸውና ለእዚህም መዘጋጀቱን ተናግሯል። በገጠር ልማትና የግብርና  ስርጸት  ትምህርት ዕጩ  ተመራቂ  የሆነችው  ሔለን  ዋጋው  በበኩሏ፣  ወደሥራ  ስትሰማራ ሕብረተሰቡን  በቅንነትና በታማኝነት  ማገልገልና  የመልካም  አስተዳደርና  የሙስና  ችግሮችን  መከላከል  ቀዳሚ  ተግባሯ  መሆኑን  አስረድታለች። በተለይ ብልሹ  አሰራሮችን  ከማስወገድ ጎን ለጎን ሥራ ፈጥሮ በመንቀሳቀስ  እራሷን፣ ቤተሰቧንና ማህበረሰቡን የሚጠቅም  ተግባር ለመፈጸም ማቀዷን ገልጻለች። በየዘርፉ የተጀመሩ የልማት እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የበኩሏን ጥረት እንደምታደርግም ጠቁማለች። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጨመዳ ፊኒንሳ በበኩላቸው እንዳሉት ሙስና፣ የመልካም አስተዳደርና  የኪራይ ሰብሳቢነት  ችግሮች  ለልማት እንቅፋት  በመሆናቸው  እነሱን  መከላከል  የእጩ  ተመራቂ  ተማሪዎች  ቀዳሚ  ተግባር መሆን አለበት። ተማሪዎቹ  በመደበኛ  የትምህርት  ጊዜያቸውና  በስልጠናው  የቀሰሙትን  ዕውቀት ወደ  ተግባር  በመለወጥ  የመንግስት ሀብትና  ንብረት ለታለመለት  ዓላማ ብቻ  እንዲውል የክትትልና  የቁጥጥር  ስራቸውን ማጠናከር  እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በዘንድሮ ዓመት በተለያዩ  የትምህርት ፕሮግራሞች ከ7 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና  በሦስተኛ ዲግሪ ያስመርቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

HTML tags are not allowed.