የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ቦርድ ዛሬ ጥር 20 ቀን 2009 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ ባካሄደው ስብሰባ የዩኒቨርሲቲው ሴኔት ለዶ/ር ፍቃዱ በየነ በ Institutional and Resource Economics የሙሉ ፕሮፌሰርነት ዕድገት እንዲሰጥ ያቀረበውን ሀሳብ አጸደቀ፡፡

ዶ/ር ፈቃዱ በየነ ቀነኢ በሚያዝያ 8 ቀን 1964 ዓ.ም ቡሪ በምትባል መንደር በጃርቴ ጃርደጋ ወረዳ ከአሊቦ ከተማ በ5 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኝ ቦታ ተወለዱ፡፡ ዕድሜአቸው ለትምህርት ሲደርስ የመጀመሪያና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት አሊቦ የትግል ፍሬ ትምህርት ቤት ተከታተሉ፡፡ ከዚያም የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሻምቡ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ1978 ዓ.ም እስከ 1981 ዓ.ም ተከታትለዋል፡፡ በ1982 ዓ.ም የሐረማያ ግብርና ዩኒቨርሲቲ በመግባት ለአራት ዓመታት ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ቆይተው በሐምሌ 1985 ዓ.ም በግብርና ምጣኔ ሀብት በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቀዋል፡፡ ከተመረቁ በኋላ በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በረዳት ምሩቅነት በግብርና ሥርፀት ትምህርት ክፍል ውስጥ በታህሳስ 1986 ዓ.ም ተቀጠሩ፡፡ ተቋሙን ለአንድ ዓመት ተኩል ካገለገሉ በኋላ የሁለተኛ ዲግሪ ስኮላርሽፕ በማግኘት በኔዘርላንድ ሀገር ዋግኒንገን ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን በመከታተል እ.ኤ.አ. በ1997 ዓ.ም በሰኔ ወር በ Management of Agricultural Knowledge Systems የሁለተኛ ዲግሪአቸውን አግኝተዋል፡፡ ከኔዘርላንድ በመመለስ ተቋሙን ለአምስት ዓመት ተኩል ካገለገሉ በኋላ እ.ኤ.አ. በመስከረም 2003 ዓ.ም German Academic Exchange Service (DAAD) ከሚባለው ድርጅት ስኮላርሺፕ በማግኘት ጀርመን ሀገር በሚገኘው ሁምቦልት ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቦርልን የሶስተኛ ዲግሪያቸውን እ.ኤ.አ በጥር 2008 ዓ.ም በ Institutional and Resource Economics አግኝተዋል፡፡ Challenges and Options in Governing Common Property በሚል ርዕስ የምርምር ፅሁፋቸው አቅርበው በከፍተኛ ማዕረግ ተመርቀዋል፡፡

ዶ/ር ፈቃዱ በየነ የሦስተኛ ዲግሪያቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ወደ ሀረማያ ዩኒቨርሲቲ በመመለስ ከማስተማር ጎን ለጎን የተለያዩ የምርምር ስራዎችን ሠርተዋል፡፡ እነኝህም በ Sustainable land management, customary pastoral land administration, food security and land use systems, and nature resource-based conflict ናቸው፡፡ በተጨማሪም ከማስተማር ጎን ለጎን ከ40 በላይ የሁለተኛ ዲግሪ እና 6 የዶክትሬት ተማሪዎችን አማክረዋል፣ የምርምር ውጤታቸውንም በታዋቂ መፅሄቶች ላይ እንዲያሳትሙ አድርገዋል፡፡ ከተለያዩ ለጋሽ ድርጅቶች ፕሮፖዛሎችን በመፃፍ የምርምር ድጋፍ አግኝተዋል፡፡ ከዚህም መካከል International Foundation for Science, Dry lands Coordination Group, Center for International Governance Innovation and centre for World Food Studies ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የምርምር ውጤቶችም በዓለም አቀፍ መፅሄቶች ላይ ታትመዋል፡፡ ከምርምር ስራዎች ባሻገር ለተለያዩ ድርጅቶች የምክር አገልግሎቶችን አበርክተዋል፡፡ ዋና ዋናዎቹ አልያንስ ፎር ግሪን ሪቮልሽን (AGRA)፣ የአለም ምግብ ፕሮግራም (WFP)፣ ቴትራቴክ ኤ.አር.አር፣ የምስራቅና የደቡባዊ አፍሪካ የማህበራዊ ሳይንስ ምርምር ድርጅት (OSSREA)፣ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በየነ-መንግስታት ድርጅት (IGAD) እና የተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት (UNDP) ናቸው፡፡

በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ከማስተማር በተጨማሪ የአፍሪካ ምጣኔ ሐብት ምርምር ኮንሰርትዮም (AERC) በሚመራቸው የድህረ-ምረቃ ፕሮግራሞች ውስጥ Institutional and Behavioral Economics እና Environmental Economics የሚባሉ የትምህርት አይነቶች (ኮርስ) በማስተማር አገልግለዋል፡፡

ከፒ ኤች ዲ ትምህርት መልስ ተቋሙን ለአራት ዓመታት ካገለገሉ በኋላ እ.ኤ.አ. በሐምሌ 2012 የተባባሪ ፕሮፌሰርነት ዕድገት አግኝተዋል፡፡ ዶ/ር ፈቃዱ ያካበቱትን የማስተማር እና የምርምር ልምድ በመጠቀም ለተለያዩ ድርጅቶች በተፈጥሮ ሐብት እንክብካቤ፣ በተፋሰስ እንክብካቤ፣ በሥርዓተ-ፆታ፣ ግብርናና ተፈጥሮ ሐብት ግንኙነት እንዲሁም ከተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ጋር ተያይዘው በሚነሱ ግጭቶች መከላከል ጉዳዮች ላይ ስልጠናዎችን ሰጥተዋል፡፡ በዚህም ረገድ በኬንያ እና ታንዛኒያ ከ26 የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ለተውጣጡ መምህራን በOSSREA ድጋፍ ባዘጋጁት የስልጠና ማንዋል በመጠቀም ስልጠናዎችን ሰጥተዋል፡፡

ዶ/ር ፈቃዱ በየነ ከሰሩት የምርምር ሥራዎች እና ካማከሩት የድህረ-ምረቃ ተማሪዎች ጋር በመሆን በአጠቃላይ 46 (አርባ ስድስት) የምርምር ፅሁፎችን በታወቁ አለም አቀፍ ሳይንሳዊ መፅሄቶች ላይ አሳትመዋል፡፡ በተጨማሪም ሶስት የውይይት ወረቀቶች (Discussion Papers)፣ 1 የስልጠና ማንዋል እና 2 የመፅሐፍት ምዕራፎችን (Book Chapters) አሳትመዋል፡፡

ዶ/ር ፈቃዱ በየነ በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ በሶስት የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ሠርተዋል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2002 ዓ.ም እስከ 2003 ዓ.ም የግብርና ሥርፀት ትምህርት ክፍል ኃላፊ ፣ ከ2008 ዓ.ም እስከ 2012 ዓ.ም ድረስ የአርብቶ አደር እና ከፊል አርብቶ አደር ተቋም በዳይሬክርነት ፣ ከዚያም ከሰኔ 2012 እስከ መጋቢት 2016 ድረስ የአስተዳደር እና ተማሪዎች ጉዳይ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን ተቋሙን አገልግለዋል፡፡

በዚህም መሰረት ዶ/ር ፈቃዱ በየነ ቀነኢ ያስመዘገቡትን ውጤት እና ለማህበረሰቡ ያበረከቱትን አስተዋፅኦ ከግምት በማስገባት የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ሴኔት መርምሮ ባፀደቀው መሰረት የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ቦርድ በ Institutional and Resource Economics የሙሉ ፕሮፌሰርነት ዕድገት ከጥር 20 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ ሠጥቷቸዋል፡፡