ለትምህርት ጥራት መጓደል የተግባር መማሪያ ቁሳቁስ እጥረት አስተዋጽኦ አድርጓል…የሐረር ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህራን

 

ረር ደብረብርሃን መስከረም 8/2008 በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ለሚታየው የትምህርት ጥራት ጉድለት የተግባር መማሪያ ቁሳቁስ እጥረትና በበቂ ሁኔታ ያለመሟላት ችግር መሆኑን በሐረማያ የኒቨርሲቲ የሐረር ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህራን ገለጹ። መምህራኑና የአስተዳደር ሰራተኞቹ በሶስተኛው ቀን ውሏቸው የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ እየተከናወኑ በሚገኙት ስራዎችና የባለድርሻ አካላት ሚና በሚሉ ርዕሶች ላይ ውይይት አካሂደዋል።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክና ፕሮግራሞች ዳይሬክቶሬት ዳይሪክተር ዶክተር ይልፋሽዋ ስዩም የትምህርት ጥራት፣ምንነትና የሚገኝበት ደረጃ ፣የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የስራ አመራር ቦርድ ሀላፊዎች፣መምህራን፣ተማሪዎችና ባለድርሻ አካላት በትምህርት ጥራት ላይ በሚጠበቅባቸው ሚና የሚል ጽሁፍ አቅርበዋል።በጽሁፉ በትምህርት ስልጠና ፖሊሲና በዘርፉ ያሉ የትምህርት ጥራት፣ተገቢነት፣ተደራሽና ፍትሃዊነት ላይ የተከናወነውንና የታየውን ችግር በዝርዝር አቅርበው ውይይት ተካሂዷል።በተለይ ባለፉት አሰርት ዓመታት እነዚህን ችግሮች ለመፍታትና የሚታዩ ክፍተቶችን ለማስተካከል መንግስት ሰፊ ስራ ማከናወኑንና አሁንም እንደቀጠለ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ በ2007 የትምህርት ዘመን ማጠቃለያ በሀገሪቱ በመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከተመረቁት ከ90 ሺህ የሚበልጡ ተማሪዎች መካከል 50 ሺህ የሚደርሱት በኢንጅነሪንግና ሳይንስ የትምህርት መስክ የተሰለጠኑ መሆናቸው ለዘላቂ ልማቱ አንጸባራቂ የሚባል ስኬት መሆኑን አስታውቀዋል።

የመምህራንን የትምህርት ደረጃ ለማሻሻል ከሰባት ሺህ የሚበልጡ መምህራንን በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የትምህርት እድል በመስጠት ከአንድ  ደረጃ ወደ ቀጣይ ደረጃ የማሳደግ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

የትምህርት ጥራትን ለማጠናከር ትምህርት ሚኒስቴር ከዩኒቨርሲቲዎች የስራ አመራር ቦርድ፣ከትምህርት ክፍል፣ ከመምህራን፣ ከተማሪዎች፣ ከኢንዱስትሪዎች፣ከማህበረሰቡ፣ከባለድርሻ አካላትና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ጋር የሰራቸውን ስራዎች በዝርዝር አቅርበዋል።

ለትምህርት ጥራት መጓደልና ለአፈጻጸሙ ችግር የሆኑና የመፍትሔ አቅጣጫ ተብለው የተቀመጡትን ስልቶችም ዶክተር ይልፋሸዋ በዝርዝር አቅርበዋል።ተሳታፊ መምህራኑ መንግስት አዳዲስ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም የመክፈትና ነባሮቹን በከፍተኛ ወጪ የማስፋፋት ስራ እያከናወነ በመሆኑ ለትምህርት ጥራት መጓደል አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።ከማስፋፋቱ ስራ ጎን ለጎን ለተቋማቱ የሚያገለግሉ የተግባር ትምህርት መስጫ ቁሳቁስ በበቂ ሁኔታ አለመሟላትና የንድፈ ሃሳብ ትምህርት ብቻ መካሄዱ ለትምህርት ጥራቱ እንቅፋት መሆኑን ገልጸዋል።

ከተሳታፊዎቹ መካከል የላቦራቶሪ ቴክኒሻን መምህር አቶ በከር ፈቶ እንደገለጹት የላቦራቶሪ መሳሪያና ቁሳቁስ እጥረት፣አጋዥ የመማሪያ መጽሀፍ ፣ለጥናትና ምርምር ስራ የሚያገለግሉ ጽሁፎችና የኢንተርኔት አገልግሎት እጥረት በተለይ አዲስ በተከፈቱ ዩኒቨርሲቲዎችና በነባሮቹም ላይ መከሰት ለትምህርት ጥራት ችግር እያስከተለ ነው።የህብረተሰብ ጤና ሳይንስ መምህር ዶክተር ጉዲና ኢጌታና አቶ ኤፍሬም ተፈራ በተመሳሳይ ሙያና የትምህርት ደረጃ ለሚያስተምሩ የሀገር ውስጥና የውጭ መምህራን የሚከፈለው የደምወዝ መጠን አለመመጣጠን የመምህራኑን የስራ ተነሳሽነት እየጎዳና ለትምህርት ጥራቱም ችግር እያስከተለ መሆኑን ገልጸዋል።የተማሪ መምህር ጥምርታ አለመመጣጠን፣ኩረጃ መስፋፋት፣የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ቁጥር መበራከት፣የሰው ሃይል እጥረትና የመምህራን ጥቅማ ጥቅም ማነስ ጥራቱ ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ በመሆኑ መንግስት ችግሩን መቅረፍ እንዳለበት ጠይቀዋል።


ውይይቱን የሚመሩት የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ስርጸት የተመራማሪዎች ቡድን አስተባባሪ ዶክተር መንግስቱ ኡርጌ እና የሐረማያ የኒቨርሲቲ የስራ አመራር ቦርድ አባል አቶ ነቢል መሃዲ መምህራኑ ያነሷቸው ጥያቄዎች በግልጽ የሚታዩ በመሆኑ ችግሩን ለማስወገድ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።መንግስት ችግሩን ለማስወገድ የሚያከናውነውንና የትምህርት ጥራቱን ለማጎልበት በሚካሄደው ስራ ላይ መምህራኑ አይነተኛ አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።በዩኒቨርሲቲው ዋና ግቢና ሐረርና ጭሮ ከተማ በሚገኙ ኮሌጆቹ ከመምህራኑና ከአስተዳደሩ ሰራተኛ ጋር በመጀመሪያው የአድገትና ትራንስፎርሜሽን አፈጻጸምና በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይ የሚካሄደው ውይይት በተቋማዊ ለውጥ ትግበራና በእስካሁኑ አፈጻጸም ላይ ውይይቱ እንደሚቀጥል ከወጣው መርሃ ግብር ለማወቅ ተችሏል።

በሌላ በኩል በሀገር አቀፍ ደረጃ ባለፉት አምስት ዓመታት የተተገበረዉ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የተርጋጋ ማይክሮ ኢኮኖሚ በመፍጠር  የዜጎችን ተጠቃሚነት ያረጋገጠ  መሆኑን የደብረብርሃን ዩኒቨርስቲ ማህበረሰብ አባላት ገልጸዋል።ከዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ አባለት መካከል አቶ መኳንንት ተስፋዉ እንደገለጹት የተጠናቀቀዉ እቅድ የልማት ፖሊሲና እስትራቴጂ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተርጋጋ ማይክሮ ኢኮኖሚ በመፍጠር ለድህነት ቅነሳዉ አስተዋጽኦ አድርጓል።በልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም ለተሳተፉ አርሶ አደርና ከተማ ነዋሪዎች የተመቻቸ የልማት ፖሊሲ ተቀርጾ በተለያየ ደረጃ በተቋቋሙ የፋይናስ ተቋማት በመበደርና በመቆጠብ ኑራቸውን እያሻሻሉ መሆኑን አስታዉቀዋል።በትምህርት ዘርፍ ተደራሽነትን በማረጋገጥ ሀገሪቱ የነበረባትን የተማረ የሰዉ ሀይልችግር በመፍታ የዜጎች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ መደረጉን ተናግረዋል።  

የዩኒቨርስቲዉ መምህር ዶክተር ሀይለየሱስ ታየ በመጀመሪያዉ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የታዩ ጠካራና ደካማ ጎኖችን ሰነዱ የፈተሸ በመሆኑ በቀጣይ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የጋራ መግባባት ላይ እንደሚደረስ ተናግረዋል።መምህር ሶደሬ ኑርዲ በእቅድ አፈፃፀሙ የሴት መምህራን ቁጥር ያነሰ በመሆኑ ሴት ተማሪዎች በጥራት በማስተማር ወደ ስራ እንዲገቡ መንግስት ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ብለዋል ።

የዩኒቨርስቲዉ ፕሬዜደንት አቶ ጌታቸዉ ተፈራ እንደገለጹት በከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሚታየውን የትምህርት ጥራትና የመልካም አስተዳደር ችግር ለማስወገድ የዩኒቨርስቲዉ ማህበረሰብ ጥራት ያለዉ የሰዉ ሀይል ቀርጾ ለማዉጣት ዉይይቱ የጋራ ግንዛቤ እንዲያዝ ያግዛል ብለዋል።

በዉይይቱ ላይ ከአንድ ሺህ 400 የሚልጡ መምህራኖችና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ለሰባት ቀናት ውይይት እንደሚያደርጉ ከመርሀ ግብሩ ለማወቅ ተችሏል።

One comment on “ለትምህርት ጥራት መጓደል የተግባር መማሪያ ቁሳቁስ እጥረት አስተዋጽኦ አድርጓል…የሐረር ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህራን

  1. Feyera Dinsa Hundessa on said:

    This news has two basic shortcomings: 1. Dr. Mengistu’s position was not written correctly; he is Director for Postgraduate Programs Directorate and Acting Vice President for Academic Affairs. 2. The paragraph that talks about Getachew Tefera as a President is totally wrong. Even at the beginning of the news, it says Debreberhan which is incorrect. Please remove the news and post it again after a thorough correction.

    Yours,
    Feyera

Leave a Reply

Your email address will not be published.

HTML tags are not allowed.