የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ ከታህሳስ 28 እስከ ጥር 5 ቀን 2009 ዓ.ም ድረስ በዩኒቨርሲቲው ዙሪያ ለሚገኙ ለስድስት የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መምህራን ለአንድ ሣምንት የህይወት ክህሎት ስልጠና ሰጠ፡፡
በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ስርዓተ ጾታ፤ልዩ ፍላጎት እና ኤች አይ ቪ ኤድስ ሜይንስትርሚንግ ዳይሬክቶሬት የኤች አይ ቪ ኤድስ ቡድን መሪ የሆኑት አቶ ይድነቃቸው ተፈራ እንደተናገሩት የስልጠናው ዋና ዓላማ በአሁኑ ጊዜ በሐገር ደረጃ ሰዎች ስለ ኤች አይ ቪ ኤድስ መዘናጋት በመፈጠሩ በበሽታው የመያዝ አጋጣሚ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ እንደሚገኝ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ስለሆነም በዚህም ወጣቱ የመጀመሪያ ተጋላጭ እንደመሆኑ ኤች አይ ቪ ኤድስ፤ስነ ተዋልዶ እና ጾታዊ ትንኮሳ ዙሪያ ግንዛቤ እንዲያገኙ ለማስቻል ብሎም በስነ-ተዋልዶ ጤና ችግር በግንዛቤ እጥረት ለከፋ ችግር እንዳይጋላጡ ለተማሪው በቅርበት ያሉት የቀለም መምህራኖቻቸው ስለሆኑ በሚሰጧቸው የምክር አገልግሎት የህይወት ክህሎታቸው እንዲዳብር ለማድረግ ከወዲሁ ለመሰራትና በተለይም ሴት ተማሪዎች ለአላስፈላጊ እርግዝና እንዳይጋለጡና ከዚህም ጋር በተያያዘ ህይወታቸውን አደጋ ላይ እንዳይጥሉ ለማስቻል መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አቶ ይድነቃቸው አክለውም ስልጠናው በዋነኛነት ከመምህራን የህይወት ክህሎት፤ ስነ ተዋልዶ፤ ጾታዊ ትንኮሳ እና በ ኤች አይ ቪ ኤድሰ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ጋር ተያይዞ በግለሰብም ሆነ በሀገር ላይ የሚያሰከትለውን ጉዳት እንዴት መከላከልና መቀነስ እንደሚቻል በተለይ ደግሞ ጾታዊ ትንኮሳን በተመለከተ በት/ቤቶች ውስጥ ችግሩ እንዳይስፋፋና የመምህራን ሚና ከፍተኛ በመሆኑ መምህራን ያገኙትን እውቀት ወደ ተማሪዎች በማውረድ ለውጥ ለማምጣት ታሰቦ የተሰጠ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የስልጠናው ተካፋዮችም በበኩላቸው ስልጠናው አቅም እንደፈጠረላቸውና እርስ በእርስም ልምዳቸውን መጋራት እንዲችሉ እድል የፈጠረላቸው መሆኑን ገልፀው ባገኙት እውቀት ተማሪዎቻቸውን ለማንቃት እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው የድጋፍ ስራም በቀጣይ በገጠር ትምህርት ቤቶች ላይ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
በስልጠናው ላይ ተካፋይ የሆኑት ከአወዳይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት፤ ከሃረማያ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት፤ ከሃረማያ መሰናዶ ት/ቤት፤ ከሃረማያ ቴክኒክ እና ሙያ ማሰልጠኛ ት/ቤት፤ ከ ዩኒቨርሲቲው ሞዴል ት/ቤት የመጡ 23 መምህራን ናቸው፡፡